ከምዕራብ ጉጂ ዞን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ በበጀት አመቱ እስካሁን 19 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገ

266

ነገሌ መጋቢት 12/2015(ኢዜአ) በበጀት አመቱ እስካሁን ከምዕራብ ጉጂ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 19  ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን የዞኑ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት መጋቢት 24 ቀንን ምክንያት በማድረግ  የ2 ሚሊዮን ብር ቦንድ ሽያጭ ለማከናወን ዞኑ የቅስቀሳ ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉንም አስታውቀዋል።

በምዕራብ ጉጂ ዞን የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ወይዘሮ ፋኖሴ ግርማ እንደ ገለጹት ዞኑ በተያዘው በጀት አመት እስካሁን ድረስ 19 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ይህም 14 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብሩ ከቦንድ ሽያጭ የተሰበሰበ ሲሆን 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብሩ ደግሞ ከስጦታ የተገኘ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ድጋፉን ያደረጉት ደግሞ ሰራተኞች፣ ባለሀብቶች፣ ነጋዴዎች፣ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡

የዞኑን ህዝብ ለድጋፍና ትብብር ይበልጥ ያነሳሳው የታላቁ ህዳሴ ግድብ 2ኛው ዙር የውሃ ሙሌት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡


 

የቡሌ ሆራ ከተማ ነዋሪና የመንግስት ሰራተኛው አቶ ገመቹ ሀለኬ እንዳሉት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሰርቶ መለወጥ በተግባር የሚያሳይና የሁላችን ተስፋ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት አመታት በራስ ተነሳሽነት የ6ሺህ 500 ብር ቦንድ መግዛታቸውን ገልጸው፤ 3ኛው ዙር የውሃ ሙሌት ደግሞ ለበለጠ ድጋፍ ያነሳሳኛል ብለዋል፡፡ 

በዚህ ዓመት ብቻ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ በልጆቼ ስም የአንድ ሺህ ብር፣ በራሴ ደግሞ "የ6 ሺህ ብር ቦንድ ገዝቻለሁ" ብለዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ከምኖርበት አካባቢ መራቁ እንጂ በጉልበት የማገዝና የመደገፍ ፍላጎት አለኝ ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የ8ሺህ ብር ቦንድ መግዛቱን የተናገረው ሌላው የከተማው ነዋሪ ወጣት ገመቹ በሪሶም ለህዳሴ ግድብ የማልከፍለው መስዋእትነት አይኖርም ይላል፡፡ 

በኢንቨስትመንት ልማትና በሀገር ገጽታ ግንባታ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ልዩ ትርጉም እንዳለውም አመልክቷል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከሀገር አልፎ ለሌላም የሚተርፍ በመሆኑ እስከ መጨረሻው ድጋፌን አላቋርጥም ሲልም ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም