ደረጃቸውን የጠበቁ የኤሌክትሮኒክስ ግብዓቶች ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲቀርቡ እየተሰራ ነው--የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት

480

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2015 (ኢዜአ) በዓለም አቀፉ ኤሌክትሮ-ቴክኒካል ኮሚሽን ውስጥ በአባልነት በመሳተፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የኤሌክትሮኒክስ ግብዓቶች ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲቀርቡ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት አስታወቀ።


 

በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ስር ለሚገኘው የኢትዮጵያ የኤሌክትሮ-ቴክኒካል ኮሚቴ አባላት የኤሌክትሮኒክስና ተዛማጅ ቴክኖሎጂዎች ደረጃቸውን የጠበቁ  እንዲሆኑ  የሚያግዝ  ስልጠና  ተሰጥቷል፡፡

ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮ-ቴክኒካል ኮሚሽን ኢትዮጵያን ጨምሮ 170 በላይ አባል አገራት ያሉት ሲሆን፤ ለኤሌክትሮኒክ፣ ኤሌክትሪካልና ተዛማጅ ቴክኖሎጂዎች ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡

በኢትዮጵያም  ቴክኖሎጂዎቹ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ብሔራዊ ኤሌክትሮ-ቴክኒካል ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወቃል፡፡ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኤሌክትሮ-ቴክኒካል ኮሚቴ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ 205 አባላት ያሉት ሲሆን፤ 34 በኤሌክትሮኒክና ኤሌክትሮ ሜካኒካል ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሠረት በቀለ እንዳሉት፤ በሀገር ውስጥ የሚመረቱና ከውጭ የሚገቡ የኤሌክትሮኒክ እና ተዛማች እቃዎች ጥራታቸውን የጠበቁ መሆን አለባቸው፡፡


 

በዚህም ኢትዮጵያ የኮሚሽኑ  አባል በመሆን ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ደረጃ በማውጣት እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህም በሀገር ውስጥ የሚመረቱት ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ የሚመረቱ ኤሌክትሮኒክ ገመዶች፣ ትራንስፎርመሮች እና ሌሎች ኤሌክትሮሜካኒካል ዕቃዎች በጥራት ተመርተው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እየዋሉ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡


 

ኢንስቲትዩቱ በዋናት የምርቶችን የጥራት ደረጃ የሚያወጣ ተቋም ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ደግሞ ምርቶች በተቀመጠው ደረጃ መሰረት መቅረባቸውን ያረጋግጣል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ፣ አገራዊና ሌሎች ደረጃዎች ላይ የተቀመጡ የጥራት መስፈርቶችን ያሟሉ 8ሺህ 800 በላይ ምርትና አገልግሎቶች የጥራት ማረጋገጫ መስጠቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት በዓለም አቀፍ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን 250ሺህ ዶላር ድጋፍ ያስገነባውን የፀሐይ ኃይል ምርቶች መፈተሻ ቤተ-ሙከራ ሥራ አስጀምሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም