ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ለመቋቋም የወሰደቻቸው ሁሉን አቀፍ እርምጃዎች የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘግብ አድርጓታል - የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ ክስተቶች የፈጠሩባትን ጫናዎች ለመቋቋም የወሰደቻቸው ሁሉን አቀፍ እርምጃዎች የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘግብ እንዳስቻላት የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ።

55ኛው የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የፋይናንስ፣ የፕላንና ኢኮኖሚ ልማት የሚኒስትሮች መደበኛ ስብሰባ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በስብሰባው በዓለም አቀፍ ያልተጠበቁ ክስተቶች፣ የማይበገር አቅም ለመገንባት እንዲሁም ድህነትና ኢ-ፍትሐዊነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችና እርምጃዎች ምን መሆን አለባቸው በሚሉ ጉዳዮች ላይ  ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ ላይ የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፤ በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያን ተሞክሮ አቅርበዋል።

የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት፣ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ክስተቶች እንደ ሌላው ዓለም ሁሉ በኢትዮጵያም የኢኮኖሚ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።


 

ከዚህ በተጨማሪ በሰሜን የኢትዮጵያ የነበረው ጦርነትና በተለያዩ አካባቢዎች የነበረው ድርቅ ለኢትዮጵያ ሌላ ፈተና ሆኖ ማለፉን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ እነዚህን ሁሉ ችግሮች ለመፍታት የፊሲካልና ሞኒተሪንግ ፖሊሲዎች ላይ የተለያዩ ማሻሻያዎች ማድረጓን አስታውሰዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዜጎች ኑሮ ላይ ጫና እንዳይፈጥር ሙሉ ለሙሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዳይዘጋ መደረጉን ያስታወሱት ሚኒስትሩ የግሉ ዘርፍ እንዳይጎዳ ጊዜያዊ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች መተግበራቸውን አንስተዋል።


 

በበሽታው ምክንያት ከፍተኛ ጫና ያደረበት የአገልግሎት ዘርፍ ተቋማት የታክስ እፎይታና ምህረት የተደረገላቸው መሆኑን ገልጸው ከባንኮች ለተበደሩ ተቋማት ገንዘብ የሚከፍሉበት ጊዜ መራዘሙን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት በምግብ ምርት ላይ የፈጠረውን ጫና ለመከላከል በአገር ውስጥ ምርት የማምረት አቅምን የማሳደግ ስራ በስፋት መከናወኑን ተናግረዋል።

በተለይም ስንዴ፣ በቆሎ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ትኩረት ተደርጎባቸው መመረታቸውን ጠቁመው በመስኖ የተከናወነው የስንዴ ልማት የላቀ ውጤት የተገኘበት መሆኑን አብራርተዋል።

ለዚህም ለአርሶ አደሮች የማዳበሪያ ግዢ ድጎማ መደረጉንና የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ወገኖች በሴፍቲኔት መርሐ-ግብር ተጠቃሚ መደረጉን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።


 

በመሆኑም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ ክስተቶች የፈጠሩባትን ጫናዎች ለመቋቋም የወሰደቻቸው ሁሉን አቀፍ እርምጃዎች የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘግብ አስችሏታል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካይ ከስድስት በመቶ በላይ እድገት እያስመዘገበች መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ የበጀት ጉድለት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የዋጋ ንረት የማክሮ ኢኮኖሚው ፈተናዎች ስለመሆናቸውም አንስተዋል።

የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠልና ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የማገገሚያ እቅድ መዘጋጀቱን ጠቅሰው ከመጀመሪያው ምዕራፍ ተሞክሮ በመውሰድ ሁለተኛ ምዕራፍ የአገር በቀል የኢኮኖሚ አጀንዳ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶችን መጠገን፣ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ድርሻ ማሳደግ፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ የአገር ውስጥ ሀብት የማሰባሰብ አቅም ማሳደግ እንዲሁም የፊስካልና ሞኒተሪንግ ፖሊሲ ማሻሻያዎች በሁለተኛው ምዕራፍ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።


 

በኢኮኖሚ አጀንዳ ትግበራው ላይ ከልማት አጋሮች ጋር ውይይት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

የማገገሚያ እቅዱን እና አገር በቀል የኢኮኖሚ አጀንዳዎች የታሰቡትን እቅዶች በቁርጠኝነት መተግበር ከተቻለ ኢትዮጵያ ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት ማስመዝገብ እንደምትችል አመልክተዋል።

በተለይም የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶችን በተለያዩ የፖሊሲ እርምጃዎች መፍትሔ ከተበጀለት ኢትዮጵያ የተሻለ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅም ይኖራታል ብለዋል።

የዲጂታል ኢኮኖሚ ትግበራም የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እና የፋይናንስ ዝውውር ላይ የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ  እንደሆነ ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የፋይናንስ፣ ፕላንና ኢኮኖሚ ልማት የሚኒስትሮች ስብሰባ በዛሬው እለትም የሚቀጥል ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም