የአካባቢ ጉዳይ ሳይንቲስቱ ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ - ኢዜአ አማርኛ
የአካባቢ ጉዳይ ሳይንቲስቱ ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
አዲስ አበባ መጋቢት 12/2015 (ኢዜአ)፦ የአካባቢ ጉዳይ ሳይንቲስቱ ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
ታዋቂው የአካባቢ ጉዳይ ሳይንቲስት ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ቤተሰቦቻቸው ለኢዜአ ተናግረዋል።
ዶክተር ተወልደ ብርሃን በአድዋ ከተማ አቅራቢያ ባለችው “አዲ-ሰላም” የተሰኘች የገጠር መንደር ነው የተወለዱት።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1955 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተቀበሉ በኋላ የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ከዌልስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።
ዶክተር ተወልደ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋካሊቲ ዲን ሆነው አገልግለዋል።
ከ1975 እስከ 1983 ዓ/ም ደግሞ የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው መስራታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ዶክተር ተወልደ ብርሃን ለብዙ ዓመታት በሚታወቁበት በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርነት ሰርተዋል።
የዕጽዋት ጄኔቲክ ሃብት ለንግድ ሲባል እንዳይለወጥና በተለይ ሰለጠኑ የሚባሉት አገሮች ገበሬው ለዘመናት ጠብቆ ያቆያቸውን የዕጽዋት ሃብቶች እንዲጠበቁም ተከራክረዋል።
ይህ መብት እንዲከበርና የእጽዋትን ጂን እየቀየሩ በፓተንት በመጠበቅ ችግር እንዳይፈጥሩ አስተባብረዋል።
ዶክተር ተወልደ ብርሃን በብዝሃ ሕይወት ጥናት እና ምርምርም ስራዎቻቸው በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችንም ማግኘት ችለዋል።
እኝህ ታላቅ የአካባቢ ጉዳይ ሳይንቲስት በዛሬው እለት በተወለዱ በ83 አመታቸው ህይወታቸው ማለፉን ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል።