የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ከጊኒ አቻው ጋር ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ወደ ሞሮኮ አቀና

703

አዲስ አበባ መጋቢት 12 2015(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ከጊኒ አቻው ጋር ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ወደ ሞሮኮ አምርቷል።

23 ተጫዋቾችን ያቀፈው ብሔራዊ ቡድኑ ትናንት ማምሻውን ወደ ካዛብላንካ ማቅናቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በኮትዲቯር አስተናጋጅነት በሚካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ከጊኒ ብሔራዊ ቡድን ጋር የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን መጋቢት 15 እና 18 ቀን 2015. በሞሮኮ ያደርጋል


 

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ 23 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ከመጋቢት 6/2015 . ጀምሮ ልምምዳቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ዋልያዎቹ ከትናንት በስቲያ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከሩዋንዳ አቻቸው ጋር ባደረጉት የአቋም መለኪያ ጨዋታ በከነዓን ማርክነህ ግብ 1 0 ማሸነፋቸው ይታወቃል።

ለደቡብ አፍሪካው ክለብ ማሜሎዲ ሳንዳውንስ የሚጫወተው አቡበከር ናስር ከጉዳቱ ሙሉ ለመሉ ባለማገገሙ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውጪ በመሆኑ በምትኩ ለኢትዮጵያ መድን የሚጫወተው ኪቲካ ጀማ መተካቱ የሚታወስ ነው።


 

በተመሳሳይ ለማጣሪያው ጨዋታ ጥሪ ተደርጎለት የነበረው የሲዳማ ቡናው አጥቂ ይገዙ ቦጋለ በልምምድ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ከብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ውጭ መሆኑ ይታወቃል።

በይገዙ ቦጋለ ቦታ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የሚጫወተው ቸርነት ጉግሳ ጥሪ ተደርጎለት ብሔራዊ ቡድኑን ተቀላቅሏል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ አራት ግብጽ፣ ከማላዊ እና ጊኒ ጋር ተደለደለ ሲሆን እስካሁን ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች በሶስት ነጥብ እና በአንድ የግብ ክፍያ ምድቡን እየመራ ይገኛል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም