የኢትዮጵያንና የየመንን ታሪካዊ ግንኙነት የሀገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በመጠቀም ማደስ ያስፈልጋል -- አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ መጋቢት 12/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያንና የየመንን ታሪካዊ ግንኙነት ለማደስ የቆየውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ከየመኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር አህመድ አዋድ ቢን ሙባረክ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።


 

በተጨማሪም፣ በተለያዩ ዘርፎች ያለውን የሀገራቱን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም ግንኙነቱን ለማደስ በሚደረገው ጥረት በቅርበት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የየመኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ሙባረክ በበኩላቸው ሀገራቱ የፖለቲካ ምክክር እንደሚያስፈልጋቸው አንስተዋል።


 

አክለውም፣ የየመን መንግስት ወደ ሀገራቸው ለመግባት ፈቃደኛ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንደሚያደርግ መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም