በክልሉ በድርቅ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች እየተደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል

240

ሀዋሳ፣ መጋቢት 11 ቀን 2015 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በድርቅ ምክንያት ለችግር  ለተጋለጡ ከ2 ሚሊዮን ለሚበልጡ ወገኖች በመንግሥትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እየተደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ።

የደቡብ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በክልሉ ለድርቅ ተጎጂዎች እየተደረገ ያለውን ድጋፍ አስመልክቶ ዛሬ ማምሻውን መግለጫ ሰጥቷል።

የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን በሰጡት መግለጫ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ባለፉት አራት የምርት ወቅቶች በቂ ዝናብ ባለመዝነቡ ከፍተኛ የምርት እጥረት ማጋጠሙን ገልጸዋል።

ይህን ተከትሎ በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ከ2 ሚሊዮን በላይ ወገኖች ለእለት እርዳታ መጋለጣቸውን ጠቅሰው፤ በርካታ የቤት እንስሳትም ለጤና ችግር መጋለጣቸውና የእንስሳት ሞትም መከሰቱንም አብራርተዋል።

የክልሉ መንግሥት ድርቅ ያስከተለውን ጉዳት ለመቋቋም በርካታ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ኃላፊዋ በመግለጫቸው አመልክተዋል።

በተለይ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሙሉ ትኩረታቸውን ሰብዓዊ ድጋፍ ላይ እንዲያደርጉ በክልሉ መንግሥት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተፈጻሚ እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥትም ወደ 100 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት መድቦ በድርቁ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ድጋፉ 24ሺህ እስር የእንስሳት መኖ፣ አስቸኳይ ድጋፍ ለሚሹ ቡርጂ፣ አማሮ፣ አሌና ደራሼን ጨምሮ ስምንት ወረዳዎች የእህል እርዳታ ያካተተ መሆኑንም ወይዘሮ ሰናይት ጠቅሰዋል።

ኃላፊዋ አክለውም ለሴራሮ፣ ባዶዋቾ፣ አቶቲ ኢሉና ማረቆ ወረዳዎች የእርዳታ እህል እየተጓጓዘ መሆኑን ተናግረዋል።  

ኮንሶና ደቡብ ኦሞ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች የፌዴራል ሥጋት ሥራ አመራርና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ ሲሆን፤ የምግብ እህል ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አስታውቀዋል።

በተለይ ያጋጠመውን የመጠጥ ውሃ እጥረት ችግር ለመፍታት በኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ስድስት የውሃ ቦቴዎችን በማሰማራት ለህበረተሰቡ የውሃ እቅርቦት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

እየተደረገ ያለው የውሃ አቅርቦት በቂ ስላልሆነ የክልሉ መንግሥት ተጨማሪ ቦቴዎችን ለማሰማራት አቅዶ በጨረታ ሂደት ላይ መሆኑን ኃላፊዋ አስረድተዋል።

በድርቁ የተጎዱ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት፣ ነፍሰጡርና  የሚያጠቡ እናቶች እንደ ጉዳታቸው መጠን በሁሉም የመንግሥት ጤና ተቋማት ነፃ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ  ነው ብለዋል።

ህጻናት በድርቁ ሳቢያ ከትምህርት ገበታቸው እንዳይለዩም የክልሉ የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የትምህርት ቤት ምገባ መጀመሩን  ወይዘሮ ሰናይት ገልጸዋል።

ከህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በመቀናጀት የተሻለ ምርት ካላቸው አካባቢዎች የእህል ግዥ በመፈጸም የትምህርት ቤት ምገባው ተጠናክሮ እንዲቀጥል  ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

እንደ ቢሮ ኃላፊዋ ገለፃ  እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ በአግባቡ መጠቀም እንዲቻልም የክልሉ መንግሥት 40 ሚሊዮን ብር  መድቦ 5 ሺህ 650 ኩንታል የቦለቄና የጤፍ ምርጥ ዘር ተገዝቶ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ነው።

በዓለም ምግብ ፕሮግራም እና በፕላን ኢንተርናሽናል በ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የተገዙ 320 ኩንታል በቆሎና 140 ኩንታል የማሽላ ምርጥ ዘር በድጋፍ መቅረቡንም ጠቅሰዋል።

ከክልሉ የተንቀሳቀሰው የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን በተለይ ድርቁ በቤት እንስሳት ላይ ያደረሰውን የጉዳት መጠንና እየተደረገ ያለውን ድጋፍ በተመለከተ የመለየትና የመከታተል ስራ እያከናወነ እንደሆነም ተናግረዋል።

ድርቁ በክልሉ ከፈጠረው ተፅእኖ አንፃር እየተደረገ ያለው ድጋፍ በክልሉ መንግሥት በቂ ነው ተብሎ እንደማይገመት ኃላፊዋ በመግለጫቸው አመለክተዋል።

በመሆኑም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ መንግሥት መዋቅሮችና ህብረተሰቡ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ወይዘሮ ሰናይት የክልሉ መንግሥት ስም ጥሪ አቅርበዋል። 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም