የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ለዉጥ ለማረጋገጥ በትምህርት ዘርፉ ለሚስተዋሉ ውስንነቶች ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት ይገባል- ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

342

ሆሳዕና፣ መጋቢት 11/ 2015 (ኢዜአ) በትምህርት ዘርፍ ለሚስተዋሉ ውስንነቶች ዘላቂ መፍትሔ በማምጣት በኢትዮጵያ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ለዉጥ ለማረጋገጥ  በተቀናጀ መንገድ የተጀመረው ርብርብ ሊጠናከር እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናገሩ፡፡

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ ጋር በመተባበር ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባውን የሊች ጎጎ አዳሪ ትምህርት ቤት የመማሪያ ህንፃ አስመርቋል።

ህንጻው የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬና በኢትዮጵያ የጃፓን ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዳሉት፤ ሀገር የሚገነባና ቴክኖሎጂ በማፍለቅ ልማትንና ፍላጎትን ሊያስተሳስር የሚችል የሰው ሀይል በሚፈራበት በትምህርት ዘርፍ ለሚስተዋሉ ውስንነቶች ዘላቂ መፍትሔ በማምጣት የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ለዉጥ ማረጋገጥ ይቻላል።

በዚህ ረገድ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ አንዱ ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን የሚተገበሩ የትምህርት ልማት ሥራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የተቀረጹ የልማት ፕሮጀክቶችን በተለያየ መንገድ እየደገፈ የሚገኘው የጃፓን መንግስት  በትምህርት ልማት ዘርፍ የሚያደርገው ድጋፍ የለውጥ ስራዎችን እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የጀመረው የአዳሪ ትምህርት ቤት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር መሆኑን አመላክተዋል።

ባለፉት ዓመታት ለትምህርት ዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ባለመሰራቱ የ2014 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ውጤት ዝቅተኛ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሯ፤ በዘርፉ ለሚስተዋሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የተጀመሩ ስራዎች እንደሚጠናከሩ ገልጸዋል።

ለዚህም ደግሞ የባለድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው እንደሃገር በትምህርት ጥራት ላይ የተጀመረውን ስራ ለማጠናከር ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል ።

በአከባቢው ለሚገኙ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚደረገው ድጋፍ አንዱ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

የድጋፉ አካል የሆነው የሊች ጎጎ አዳሪ ትምህርት ቤትን በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ ጋር በመሆን ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመማሪያ ክፍሎች ማስፋፊያ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሊደረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በግብዓት የማሟላት ስራ ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቱ በ2013 ዓ.ም ከ 9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል  80 ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ስራውን የጀመረ ሲሆን በቀጣይም ብቁ የሰው ሀይል ከማፍራት አንጻር የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በበኩላቸው የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እየደገፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በሊች ጎጎ ትምህርት ቤት የተደረገው ድጋፍም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰዉ ሀብት ልማት ስራን ለማሳደግ የሚደረገው ድጋፍ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁት የመማሪያ ክፍሎች የትምህርት ቤቱን መምህራንና ተማሪዎች የመማር ማስተማር ሂደት የሚደግፉ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም