የአፍሪካ ፋይናንስ ተቋማት ለጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚያደርጉትን የፋይናንስ አቅርቦት ሊያጠናክሩ ይገባል- የአፍሪካ ልማት ኤጀንሲ

521

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2015(ኢዜአ)፦የአፍሪካ ፋይናንስ ተቋማት ለጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚያደርጉትን የፋይናንስ አቅርቦት  እንዲያጠናክሩ የአፍሪካ ልማት ኤጀንሲ ጥሪ አቀረበ።

በአፍሪካ ሕብረት ልማት ኤጀንሲ አማካኝነት በሚተገበረው የ"100 ሺህ ጥቃቅን፣ መካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኢኒሼቲቭ" ትግበራ ዙሪያ የአባል ሀገራት ባለድርሻ አካላት ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

ኢኒሼቲቩ በዋናነት በኢንተርፕራይዞች ትምህርትና ስልጠና፣ በፋይናንስ አቅርቦት እና የገበያ ቦታ ማመቻቸት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ነው፡፡

የአፍሪካ ልማት ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያሳየው ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በአፍሪካ 90 በመቶ የንግድ እንቅስቃሴ ድርሻ ሲኖራቸው 60 በመቶ የስራ ዕድል በመፍጠር  ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ እያደረጉ የሚገኙ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ናቸው።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን እ.ኤ.አ በ2019 ኢንተርፕራይዞች ለአንድ ሚሊዮን ዜጎች ስራ ዕድል እንዲፈጥሩ የማድረግ አህጉር አቀፍ ዘመቻ ይፋ ያደረገ ሲሆን ዘመቻውም ከ2063 ልማት አጀንዳዎች ጋር የተጣጣመ ነው።

በአፍሪካ ልማት ኤጀንሲ የሰው ሀብት ልማት ተጠባባቂ ኃላፊ ዶክተር ጃኔት ብሪሃንጋ በተለይም ለኢዜአ እንዳሉት፤ ጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለአፍሪካ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ናቸው።

ኢኒሼቲቩ እነዚህን ኢንተርፕራይዞች በትምህርትና ስልጠና፣ በፋይናንስ አቅርቦት እና በገበያ ቦታ በመደገፍ ውጤታማ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ አተገባበሩ ግን የራሱ ፈተናዎች እንዳሉት ጠቁመዋል።

እስካሁን ከ55 የአፍሪካ አባል ሀገራት መካከል በሁለት ዙር በ20 ሀገራት ከ10 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞችን መደገፍ መቻሉን ገልጸው፤ ዋነኛው ፈተናም ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገራትም ሆነ አህጉራዊ የፋይናስ ተቋማት መሬት ላይ ወርደው ኢንተርፕራይዞችን ከመደገፍ አንጻር ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉባቸው ነው የተናገሩት።

በዚህም የፋይናንስ ተቋማት ተገማች፣ ተመጣጣኝ እና የተራዘመ ብድር ስርዓት በመዘርጋት ኢንተርፕራይዞችን በፋይናንስ አቅርቦት ሊደግፏቸው እንደሚገባ ነው የጠየቁት።

በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ንግድ ስራ ድጋፍ ወይም 'ሲድ' የተሰኘው ድርጅት የምሥራቅ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ፍራንክ ዋሩይንጊ፤ 80 በመቶ አፍሪካውያን ስራ ዕድል ፈጣሪ ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲያሻሽሉ እና የገበያ መዳረሻቸው እንዲሰፋ የሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል። 

ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ እንደ አህጉር ጥረቶች ቢኖሩም የፋይናንስ ተቋማት ግን  ተገቢውን ድጋፍ እያቀረቡ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ በሞሪሺየስ የኢንዱስትሪ ልማት ሚኒስቴር የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ዘርፍ ምክትል ዋና ፀሐፊ አክሻይ ጀዎላል፤ ኢንተርፕራይዞች በፋይናንስ እና ምቹ የገበያ ቦታ በማመቻቸት በዘላቂነት ሊደገፉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።


 

ይህም የአፍሪካን ኢኮኖሚ እድገትን በማሳለጥ ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ነው የተናገሩት፡፡

'አፍሪላብስ' የተሰኘው የናይጀሪያ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ፈሊሲታ አኩ በበኩላቸው፤ መንግስታዊ፣ መንግስታዊ ያልሆኑና የግል ተቋማት በአፍሪካ ከስራ ዕድል ፈጠራ ባሻገር ኢንተርፕራይዞችን መደገፍ ላይ በትብብር እንዲሰሩ ጠይቀዋል።


 

የአፍሪካ አገራት የሚያዘጋጇቸው ፖሊሲዎች ይህንን ታሳቢ ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባም ነው የጠየቁት፡፡

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም