የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ 2 ሺህ የከተማ አውቶብሶችን ማምረት የሚያስችለውን ስምምነት ከቻይናው ዮቶንግ ኩባንያ ጋር ተፈራረመ

279

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ 2 ሺህ የከተማ አውቶብሶችን ማምረት የሚያስችለውን ስምምነት ከቻይናው ዮቶንግ ኩባንያ ጋር ተፈራረመ።

ስምምነቱን የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ እና የዮቶንግ ኩባንያ የኢትዮጵያ ተወካይ ሉ ሻይ ተፈራርመዋል፡፡

አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በስምምነቱ መሰረት በኢትዮ ኢነጂነሪንግ ግሩፕ ስር የሚገኘው የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ኢንዱስትሪ 2 ሺህ አውቶብሶችን ማምረት የሚያስችለውን ግብዓት ከኩባንያው የሚያገኝ ይሆናል፡፡

ይህም የኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም በማሻሻል ረገድ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

አውቶቡሶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመርተው በአዲስ አበባ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ጠቅሰው፤ ይህም የመዲናዋን የትራንስፖርት ችግር ትርጉም ባለው መልኩ ያቃልላሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡


 

የዮቶንግ ኩባንያ በኢትዮጵያ ተወካይ ሉ ሻይ በበኩላቸው ስምምነቱ አውቶብሶችን ለመገጣጠም የሚሆን ግብዓት ከማቅረብ ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በቀጣይም መሰል በሆኑ ተግባራት በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በስምምነቱ መሰረት የሚገጣጠሙት አውቶብሶች 40 መቀመጫ ያላቸው ሲሆን በተጨማሪም ለአካል ጉዳተኞች፣ ዊልቸር ተጠቃሚዎችና ለአቅመ ደካሞች እንዲጠቀሙባቸው ምቹ ሆነው እንደሚዘጋጁ ገልጿል።

ካሜራዎችን ጨምሮ ዘመናዊ የቁጥጥር መሳሪያዎች እንደሚገጠምላቸው ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም