የሲዳማ ክልል ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገለጸ

357

ሀዋሳ መጋቢት 11/2015 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ለበጋ መስኖና ለበልግ እርሻ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

የምክር ቤት አባላት የህዝቡን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ አስፈጻሚ አካላትን በአግባቡ መከታተል እንዳለባቸው የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አስታውቀዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ ዛሬ በተጀመረው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች እንዳሉት በአሁኑ ሰዓት የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ስራዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

በክልሉ በግብርናው ዘርፍ በበጋ መስኖ 67 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴና በተለያዩ የጓሮ አትክልቶች እየለማ እንደሚገኝ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ በመስኖ የለማው ምርት ወደ ገበያ ሲገባ የዋጋ ንረቱን ማቃለል ያስችላል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በገበያ ያለው የዋጋ ንረት የተከሰተው በተወሰነ ደረጃ በተፈጠረው የምርት ስርጭትና ዝውውር መስተጓጎል ምክንያት እንደሆነ ጠቁመዋል።

የስርጭት ችግሩን ከመቅረፍ ጎን ለጎን በግብርና መስክ ምርትና ምርታማነትን በሚያሳድጉ ስራዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በሌላ በኩል በክልሉ የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ በተያዘው ዓመት 51 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ባለፉት ሰባት ወራት ለ30 ሺህ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

የመልካም አስተዳደር ችግር ከመቅረፍ አንጻርም በክልሉ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ የአሰራር ክፍተቶችን በማረም ፍትሃዊ አገልግሎት መንግስታዊ ተቋማት እንዲሰጥ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በዋናነት በፍትህና ጸጥታ ዘርፉ ዙሪያ ከህዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን መሰረት በማድረግ በተያዘው ወር አጠቃላይ የክልሉን የፖሊስ መዋቅር በመገምገም የማጥራት ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ የፍትህ ተቋማት በተናጠል ከሚያከናውኑት ተግባር ባለፈ ፍርድ ቤቶች፣ አቃቤያነ ህጎች፣ መርማሪ ፖሊሶች በጋራ ተቀናጅተው እንዲሰሩ ማድረግ የሚያስችል ኮሚቴ መዋቀሩንና ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።


 

የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ በበኩላቸው የምክር ቤት አባላት የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ አስፈጻሚ አካላትን እየተከታተሉ ነው ብለዋል።

እያንዳንዱ አስፈጻሚ አካል የሚያከናውናቸው ተግባራት በህዝብ ዘንድ ቅሬታ እንዳያሳድሩ በተገቢው መንገድ አገልግሎት መስጠታቸውን በመከታተልና በመገምገም ረገድ የምክር ቤቱ አባላትና ቋሚ ኮሚቴዎች ትልቅ ሀላፊነት እንዳለባቸውም አመላክተዋል።

በተጨማሪም የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እንዲሁም ህግ ወጥ ነጋዴዎችን በመቆጣጠር ረገድ ምክር ቤቱ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ጉባኤው በሁለት ቀናት በሚኖረው ቆይታ የክልሉ መንግስት የሰባት ወር አፈጻጸም ሪፖርትን በመገምገም፣ የተለያዩ ሹመቶችን በመስጠትና አዋጆችን በማጽደቅ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም