የአፍሪካ አገራት ኢኮኖሚያዊ  ፈተናዎችን ለማለፍ  ቀጣናዊ እና አህጉራዊ የግብይት ሰንሰለት መዘርጋት ላይ መስራት አለባቸው 

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2015(ኢዜአ)፦ አፍሪካ ለሚያጋጥሟት ኢኮኖሚያዊ  ፈተናዎች ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ጠንካራ ቀጣናዊ እና አህጉራዊ የግብይት ሰንሰለት መዘርጋት እንደሚገባት ተገለጸ።

የአፍሪካን የገቢ መሰብሰብ አቅም እየፈተነ የሚገኘውን ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር መከላከል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተመልክቷል።   

55ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የፋይናንስ ፣ ፕላኒንግ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች መደበኛ ስብስባ ዛሬ በሚኒስትሮች ደረጃ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ስብሰባው እየተካሄደ የሚገኘው “የአፍሪካ መልሶ ማገገም እና ለውጥ በማፋጠን ኢፍትሐዊነትና ተጋላጭነትን መቀነስ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው።  

በስብሰባው መክፈቻ ላይ የኮሚሽኑ አባል አገራት የፋይናንስ፣ እቅድ እና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች እና ተወካዮች፣ የተመድ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የልማት አጋሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የኢኮኖሚ ልማት፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ኮሚሽነር አልበርት ሙቻንጋ  በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር አፍሪካ ባለፋት ሁለት አስርት ዓመታት ውጤታማ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧን አንስተዋል።  

የእዳ ቀውስ፣ አየር ንብረት ለውጥ የፈጠረው ድርቅ እንዲሁም ሌሎች ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የኢኮኖሚ ስኬቶችን ወደ ኋላ የመመለስ ስጋት መፍጠራቸውን አመልክተዋል። 


 

የገጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ሕዝብን ማዕከል ያደረገ የለውጥ እና የማገገሚያ ስትራቴጂ ያስፈልጋል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ።   

በአፍሪካ የሚፈጠሩ የስራ እድሎች ድህነትን የሚቀርፉ፣ ሁሉን አቀፍ እና የሰራተኞች ደህንነት የጠበቁ መሆን አለባቸው ሲሉም ነው ያሳሰቡት።  

አፍሪካ በየጊዜው የሚገጥሟትን ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ፈተናዎች ለመቋቋም የዓለም ግብይት ሰንሰለት መሻሻልን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን የራሷን ቀጣናዊ እና አህጉራዊ የግብይት ሰንሰለት መዘርጋት እንደሚገባት ተናግረዋል።   

ለዚህም የገበያ አማራጭ ማስፋት፣ ለጥናትና ምርምር ትኩረት መስጠት፣ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች በስፋት ማምረት፣ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ማስተዋወቅ እና የምርት ስያሜ (ብራንድ) እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚያስፈልግም ነው ኮሚሽነሩ ያብራሩት።  

የአፍሪካ አገራት ለገቢ አሰባሰብ ተግዳሮት የሆነውን ሕገወጥ የፋይናንስ ዝውውር መከላከልና የአገር ውስጥ ሀብት የማሰባሰብ አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።  

አገራት ለአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ተፈጻሚነት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አስረድተዋል።

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አፍሪካን ጨምሮ በማደግ ላይ ለሚገኙ አገራት ያላቸውን የፋይናንስ አቅርቦት ማሳደግ ይገባቸዋል ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ለሕብረቱ አባል አገራት ኢኮኖሚያዊ እድገት እና ዘላቂ ልማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር በትብብር እንደሚሰራ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

የሚኒስትሮች ስብሰባው ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ የወጣው መርሃ ግብር ያስረዳል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም