ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ ወዳጅነታቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ- አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ

281


አዲስ አበባ መጋቢት 11/2015 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኮሪያ ወዳጅነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ፡፡

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ይህን ያሉት ለምክር ቤቱ አባላት በተሰጠው ስልጠና ማጠቃለያ ላይ ነው፡፡  


 

በደቡብ ኮሪያ የሚገኘው እና በአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ስልጠና በመስጠት የሚታወቀው አይ ዋይ ኤፍ የተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት ለምክር ቤቱ አባላት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስልጠና ሰጥቷል።

ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ በጤና፣ በግብርና፣ በኢኮኖሚና በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውን አፈ ጉባኤው አስታውሰዋል።

አያይዘውም በአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ያተኮረውና አይ ዋይ ኤፍ የተሰኘው ድርጅት የሚሰራው ሥራ የ"ይቻላል አስተሳሰብን ለማዳበር" ይረዳል ብለዋል።

አፈ-ጉባኤ ታገሰ በአስተሳሰብ ዙሪያ የተሰጠው ስልጠና የግል ህይወትን፣ አካባቢንና ሀገርን ለመለወጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም አመላክተዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ እና ኮሪያ በዘርፉ ተቀራርበው ሊሰሩ እንደሚገባ አንስተዋል።

የአይ ዋይ ኤፍ መስራች እና ለምክር ቤቱ አባላት ስልጠና የሰጡት ዶክተር ፓርክ ይህን ስልጠና ለማስፋት እና በኢትዮጵያ ትኩረት አድርገው ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ ለዚህ ስልጠና ትኩረት ሰጥቶ ኢትዮጵያንና ኮሪያን ለማቀራረብ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን ከምክር ቤቱ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም