በኢትዮጵያና በኮሪያ ሪፐብሊክ መካከል ለግብርና መካናይዜሽን የልህቀት ማዕከል ግንባታ የሚውል የ14 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ስምምነት ተፈረመ

255

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2015(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ እና በኮሪያ ሪፐብሊክ መከካከል ለግብርና መካናይዜሽን የልህቀት ማዕከል ግንባታ የሚውል የ14 ነጥብ 8 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር /የ794 ሚሊዮን ብር/ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት በበይነ መረብ በተከናወነ ስነ-ስርአት ተፈረመ።

የፋይናንስ ድጋፉ ዓላማ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትንና በሃገር ውስጥ የሚመረቱትን ምርቶች ወደ ተገልጋዩ ከመድረሳቸው በፊት የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው ስለመመረታቸው የሚያረጋግጥ ማዕከል መገንባት ነው።

በዚህም በአሁኑ ወቅት በጥራትና ብቃት ማነስ ምክንያት በተጠቃሚው ላይ እየደረሰ ያለውን ኪሳራ በመቀነስ በሃገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይም ያለውን አሉታዊ ተጽእኖና ወደፊትም ሊከሰት የሚችለውን ጉዳት በማስቀረት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማፋጠን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሆነም ተገልጿል።

በፕሮጀክቱ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት የመካናይዜሽን ስልጠና ፍተሻና ምርምር ማእከል ማቋቋም፣ በክልሎች ደረጃ የኦፕሬሽን እና ጥገና ማእከል ማቋቋም፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችና ማከናወን፣ የማስተዋወቅና የሰርቶ ማሳያ ተግባራትን ማከናወን ፣ የማእከሉን ኦፕሬሽን ሞዴል ማዘጋጀትና ለፕሮጀክቱ እገዛ ለሚያደርጉ ባለሙያዎች ድጋፍ መስጠት ናቸው፡፡

የኦፕሬሽንና የጥገና ማእከላቱ በአዲስ አበባ ቃሊቲ፣ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ፣ በአማራ ክልል ቡሬ ከተማ፣ በደቡብ ክልል አላባ ከተማ እንደሚቋቋሙ ከገንዘብ ሚኒስቴር ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የፋይናስ ድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሰመሬታ ሰዋሰውና ሚስተር ቺዩን ፓርክ የደቡብ ኮርያ የቴክኖሎጂ ልህቀት ኢኒስቲቲዩት ዳይሬክተር ጄነራል ፈርመውታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም