የግብርና ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ከ394 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የግብርና ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ከ394 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2015(ኢዜአ)፦ የግብርና ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በኦሮሚያ፣ ደቡብና ሱማሌ ክልሎች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከ394 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ድጋፉን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ሚኒስቴሩ ድጋፉን ያደረገው በዓለም ባንክ፣ አውሮፓ ህብረት እና የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት ጋር በመተባበር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተቋማቱ ከሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ተቀንሶ ከተደረገው ከ394 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ገልጸው፤ በዚህም ለኦሮሚያ ክልል 170 ሚሊዮን፤ ለሱማሌ ክልል 160 ሚሊዮን እንዲሁም ለደቡብ ክልል 64 ሚሊዮን ብር እንደሚከፋፈል ተናግረዋል፡፡
ድጋፉ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚሆን የምግብ እህል ግዥ እንደሚውልም ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም አሁን ላይ በድርቅ በተጎዱ አንዳንድ አካባቢዎች ዝናብ መዝነብ መጀመሩን ተከትሎ ለእንስሳት መኖ፣ ዘር እና መድኃኒት ግዥ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በቀጣይ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣም አረጋግጠዋል፡፡