የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ስርቆት ለከፍተኛ ወጪና የኃይል መቆራረጥ ችግር እየዳረገ ነው... የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል 

265

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2015 (ኢዜአ) የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ስርቆት መንግስትን ለከፍተኛ ወጪ ከማድረጉ ባለፈ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የኃይል መቆራረጥ ችግር እያስከተለ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።   

በዘርፉ እየተከናወኑ ስላሉ  የልማት ሥራዎችንና እና እያጋጠሙ  ያሉ ተግዳሮቶችን በማስመልከት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

መንግሥት በዘርፉ እያከናወናቸው ያሉ የልማት ሥራዎች  በርካቶች መሆናቸውን ያነሱት አቶ ሞገስ፤ የመሰረተ-ልማት  ስርቆት ደግሞ ፈተና እየሆነ መጥቷል ብለዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተለይም የኤሌክትሪክ ተሸካሚ መስመሮች ላይ እየተፈጸመ ያለው ስርቆት ለኅብረተሰቡ ኃይል ተደራሽ በማድረግ ሂደት ላይ እንቅፋት መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻር ባለፈው ዓመት ብቻ ዝርፊያ የተፈጸመባቸውን የኤሌክትሪክ ተሸካሚ መስመሮች ለመጠገን ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አቶ ሞገስ ጠቅሰዋል።

የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ስርቆት መንግስትን ለከፍተኛ ወጪ ከመዳረጉ ባለፈ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የኃይል መቆራረጥ ችግር እያስከተለ ነው ብለዋል። 

በዚህም ምክንያት ለአዳዲስ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች መዋል ያለበት ገንዘብ ለጥገና እየዋለ በመሆኑ በዘርፉ ልማት ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ እየደረሰ ያለውን  ስርቆት ለመከላከል ሕብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚው ሕዝብ አሁን ላይ 35 በመቶ ብቻ መሆኑን የጠቀሱት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ፤ ተደራሽነቱን ለማስፋት የማስፋፊያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሁን ያለውን 5 ሺህ 256 ሜጋ ዋት ኃይል በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ሀገራዊ የኃይል ማምረት አቅምን  በእጥፍ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከውኃ ከ45 ሺህ  ሜጋ ዋት በላይ፣ ከእንፋሎት ከ10 ሺህ ሜጋ ዋት እንዲሁም ከፀሐይ ኃይል ከ1 ጊጋ ዋት በላይ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት ይነገራል።

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም