ቀጥታ፡

የአፍሪካ ሀገራት ለቀጣናዊ ውህደት መሳካት የመሰረተ ልማት ትስስርን ሊያፋጥኑ ይገባል- የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2015(ኢዜአ)፦የአፍሪካ ሀገራት ለቀጣናዊ ውህደት መሳካት የመሰረተ ልማት ትስስርን ሊያፋጥኑ እንደሚገባ በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) የቀጣናዊ ውህደትና የንግድ ዘርፍ ዳይሬክተር ስቴፈን ካሪንጊ ገለጹ።

የአፍሪካ የነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነትን ትግበራን ማሳለጥ ለቀጣናዊ ትብብር መጠናከር ወሳኝ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) የቀጣናዊ ውህደትና የንግድ ዘርፍ ዳይሬክተር ስቴፈን ካሪንጊ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነቱን ተከትሎ ኢትዮጵያን ጨምር በአፍሪካ የንግድና ገበያ ትስስር እየተጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።

የቀጣናዊ ውህደት የገበያ ልውውጥን፣ የመሰረተ ልማት ትስስርን፣ የህዝብ ለህዝብ ማህበራዊ ግንኙነትን፣ ጨምሮ በርካታ ዘርፎች እንዳሉት ጠቅሰዋል።

በአፍሪካ ቀጣናዊ የሀገራት ውህደት በየመስኩ በተለያየ ምዕራፍ ላይ የሚገኝ እድገት እያሳየ መምጣቱን አንስተዋል።

በመሆኑም ነጻ የንግድ ቀጣናው በፈጠረው ዕድል የአፍሪካ ሀገራት ለመሰረተ ልማት ትስስር ትኩረት በመስጠት የቀጣናዊ ውህደትን በማፋጠን በትብብር የጋራ ተጠቃሚነትን ሊያሳድጉ ይገባል ነው ያሉት።

በነጻ የነግድ ቀጣና ስምምነቱ መሰረት የሚደረግ የእቃዎችና አገልግሎቶች የንግድ ልውውጥ ያለ መሰረተ ልማት ትስስርና ቀጣናዊ ውህደት ሊሳካ አይችልም ብለዋል።

ይህም በመሆኑ በቀጣናው ከሚደረግ የንግድና ገበያ ልውውጥ የሚፈለገውን ያህል ጥቅም ማግኘት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

አህጉራዊ ውህደትን ማፋጠን ለአፍሪካ ልማት ወሳኝ በመሆኑ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ማፋጠን ይገባል ብለዋል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝና የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት አፍሪካውያን የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ሀብቶችን ለመሰረተ-ልማት ዝርጋታ እንዳያውሉ እንዳስተጓጎላቸው ጠቅሰዋል።

በመሆኑም አህጉራዊ ውህደትና ትብብርን ለማጠናከር ለመሰረተ ልማት ትስስር ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ጊዜው አሁን ነው  ብለዋል።

የአፍሪካ ሀገራት ለቀጣናዊ ውህደት መሳካት የመሰረተ ልማት ትስስርን ሊያፋጥኑ ይገባልም ነው ያሉት የቀጣናዊ ውህደትና የንግድ ዘርፍ ዳይሬክተሩ ስቴፈን ካሪንጊ። 

የአንድ አፍሪካ የአየር ትራንስፖርት አፍሪካን በማስተሳሰር ረገድ ከፍተኛ አቅም እንዳለውም ነው የጠቆሙት።

በመሆኑም የአፍሪካ መንግሥታት የአፍሪካ አየር መንገዶች በየሀገራቱ አውሮፕላን ማረፊያዎች በአንድ የአየር ትራንስፖርት ስር እንዲሰሩ በመፍቀድ ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው የሰዎችን፣ የሸቀጥና የአገልግሎት ዝውውርን እንዲያፋጥኑ መፍቀድ አለባቸው ብለዋል።

በአፍሪካ ነጻ የእንቅስቃሴ ስምምነትን ሁሉም ሀገራት አጽድቀው ወደ ተግባር መለወጥ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በአፍሪካ ያለ ቪዛ መንቀሳቀስን የፈቀዱ የተወሰኑ ሀገራት መኖራቸውን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ 25 ሀገራት የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን የተወሰኑት ደግሞ የኤሌክትሮኒክ ቪዛ አገልገሎትን መስጠት መጀመራቸው የሚበረታታ ነው ብለዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም