ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ባለፉት 2 ሳምንታት ያጋጠመው የኃይል መቆራረጥ በመጋቢ መስመሮች ባጋጠመ ችግር ነው--የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎትክ

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2015 (ኢዜአ) ባለፉት ሁለት ሳምንታት ያጋጠመው የኃይል መቆራረጥ በነበረው ነፋሻማና ዝናባማ የአየር ፀባይ 50 መጋቢ መስመሮች ላይ ብልሽት በማጋጠሙ የተከሰተ መሆኑን የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ተቋማቱ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ላጋጠሙ ችግሮች ይቅርታ ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ገበየሁ ሊካሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በነበረው የኃይል መቆራረጥ በተቋማት እና በግለሰቦች ዘንድ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።

የኃይል መቆራረጡ በዋናነት በአራት መሰረታዊ ምክንያቶች እንደሆነም አስረድተዋል።

የወቅቱ አየር ሁኔታ፣ ከተማ ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ የመልሶ ግንባታ ሥራዎች፣ በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ እየተከናወነ ያለ የጥገና ሥራና በመሰረተ-ልማት ላይ በሚደርሱ ጉዳቶች መሆኑን ተናግረዋል።

መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በጣለው ዝናብ ምክንያትም ካሉት 137 መጋቢ መስመሮች ውስጥ 50 በሚሆኑት ላይ ብልሽት ማጋጠሙን ጠቁመዋል።

አገልግሎቱ የኃይል አቅርቦቱ ወደነበረበት እንዲመለስ እና አስተማማኝ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በኃይል መቆራረጥ ምክንያት ላጋጠመው ችግር ለተገልጋዮች ይቅርታ ጠይቀዋል።


 

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ፍቃዱ ዘለቀ በበኩላቸው፤ ባለፉት ሦስት ሳምንታት ከወትሮው በተለየ የውሃ አቅርቦት መቆራረጥ ማጋጠሙን ጠቅሰዋል።

በኃይል መቆራረጥ ምክንያት የነበረው የፈረቃ ሥርጭት ላይ መዛባት መፈጠሩንም ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ በቀን እስከ 725ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ እያመረተ እንደሚገኝና አሁንም የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም መኖሩን አንስተዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ወደ ሥራ መግባታቸውንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም