የአፍሪካን ሃብት በማልማት ዜጎቿን ከድህነት ለማውጣት የሁላችንንም የጋራ ትብብርና ጥረት ይጠይቃል- የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ

340

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2015 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካን ሃብት በማልማት ዜጎቿን ከችግርና ከድህነት ለማውጣት የሁላችንንም የጋራ ትብብርና ጥረት ይጠይቃል ሲሉ የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ፔድሮ በበኩላቸው በአፍሪካ የምጣኔ ሃብት እድገት ለማስመዝገብ ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

55ኛው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) የፋይናንስ፣ ምጣኔ ሃብትና ፕላን ሚኒስትሮች ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ፤ የአፍሪካን የምጣኔ ሃብት እድገት በማስተጓጎል ረገድ ፈተና እየሆኑ የመጡ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ክስተቶችን አንስተዋል።


 

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የሩስያና ዩክሬን ጦርነትና የአየር ንብረት ለውጥ አሁን ላይ የአፍሪካ የምጣኔ ኃብት እድገት ፈተና በመሆን ዜጎቿን ለችግር መዳረጋቸውን አብራርተዋል።

በመሆኑም በአፍሪካ ላይ ተጽእኖ እያሳደሩ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና የአፍሪካን ሃብት በማልማት ዜጎቿን ከችግርና ድህነት ለማውጣት የጋራ ጥረትና ትብብራችን ግድ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

አፍሪካ ዕድገትና ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ እምቅ ሃብትና ሰፊ አማራጮች ያሏት በመሆኑ በጋራ ከሰራን ከችግርና ድህነት መውጣት እንችላለን ብለዋል።

ለልማት የሚያስፈልገውን ፋይናንስ በራስ አቅም ለመሸፈን የገቢ አሰባሰብን ማዘመንና ፓሊሲን ማሻሻል ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል።

ለአፍሪካ ዘላቂ ልማት ጠንካራ ምጣኔ ሃብትና አስተማማኝ የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት ያስፈልጋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።

ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ እየሰራች ያለውን ስራ እና በሌሎች መስኮች የጀመረቻቸውን የለውጥ እርምጃዎች አብራርተዋል።


 

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ፔድሮ በበኩላቸው በአፍሪካ የምጣኔ ሃብት እድገት ለማስመዝገብ ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የአፍሪካ የምጣኔ ሃብት እድገት ስኬታማ ማድረግ የሚቻለው የራስ ሃብትን በማልማት ጥቅም ላይ ማዋል ሲቻል መሆኑንም ገልጸዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም