የክልሉን ሴቶች በሁሉም መስክ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው - የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን ሴቶች በሁሉም መስክ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው - የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ቢሮ
ሐረር መጋቢት 11/2015 (ኢዜአ) የክልሉን ሴቶች በሁሉም መስክ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምብሩ ገለጹ።
የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች በመስክ ተጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምብሩ እንደተናገሩት በክልሉ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ ነው።
እንደ ሃላፊዋ ገለጻ በተለይም በክልሉ የሴቶችን ገቢ ከማጎልበት አኳያ 80ሺህ የሚደርሱ ሴቶችን በልዩ ኢንሼቲቭ በተለያዩ የስራ ዘርፍ በማሰማራት ተጠቃሚ የማድረግ ስራ መጀመሩን ነው የተናገሩት።
በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የተጀመረው ኢንሼቲቭ ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከማድረጉ ባለፈ የአገር ኢኮኖሚን የማሳደግ ሚናው የላቀ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።
ወይዘሮ ጀሚላ አክለውም በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ የሚገኙ ሴቶች በኢኮኖሚ እራሳቸውን ለማጎልበት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በከብት እርባታ፣ በወተት ማቀነባበርና በሌሎች መስኮች እያከናወኗቸው የሚገኙት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን በመስክ ጉብኝት መመልከታቸውን ተናግረዋል፣
የክልሉ መንግስትም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በማከል።
በዞኑ ከተደራጁት ከ800ሺህ በላይ ሴቶች ውስጥ 500ሺህ ያህሉ በተለያዩ የስራ ዘርፍ ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ያሉት ደግሞ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሲስተር መርየማ መሐመድ ናቸው።
በዚህም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በብድርና ቁጠባ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና በሌሎች በማህበር ተደራጅተው በመንቀሳቀስ መኖሪያ ቤት በመስራትና ንብረት በማፍራት እራሳቸውን እያስተዳደሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በዞኑ ሐረማያ ወረዳ ኢፋ ኦሮሚያ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሳፍያ አብዲ በበኩላቸው በተናጠል ከሚደረግ እንቅስቃሴ በ10 ሰው ማህበር ተደራጅተው በስንዴ ልማት መሰማረታቸውን ተናግረዋል።
አሁን ላይ የደረሰ የስንዴ ማሳ እንዳላቸው ገልጸው፤ በማህበር ተደራጅተው ወደ ስራው ከገቡ ወዲህ ተሸከርካሪ እንዲሁም ጄኔሬተር ገዝተው ስራቸውን እያስፋፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ከጠባቂነት ተላቀው ከወንዶች እኩል ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል።
በስንዴ ልማት ተጠቃሚ እየሆኑ መሆናቸውን የተናገሩት ሌላዋ የኢፋ ኦሮሚያ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ኪሚያ አብዶሽ ናቸው።
ዝናብ ሲያጥር የበለጠ እንደሚያስቸግር ተናግረው፤ አሁን ዝናብ በማግኘታቸው በዚህ ዓመት ጥሩ ጥቅም እንደሚያገኙ ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ቢሮው ከጉብኝቱ በተጓዳኝ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ኩርፋ ጨሌ ወረዳ በዝናብ እጥረት ችግር ላጋጠማቸው 500 ሴቶች የምግብና የቤት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።