ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እየመጣ ያለው ሰላምና መረጋጋት በዲፕሎማሲ እና በኢኮኖሚ ልማት አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2015(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ እየመጣ ያለው ሰላምና መረጋጋት በዲፕሎማሲ እና በኢኮኖሚ ልማት አበረታች ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

7ኛው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አገራዊ የቅንጅት መድረክ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

መድረኩ "የጸረ-ኮንትሮባንድ ሥራችን በማጠናከር የአገራችን የማህበረ ኢኮኖሚያዊ ልማትና ሰላም እናረጋግጣለን፥ ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራርን በማስፈን የአገራችንን ልማት እናፋጥናለን" በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ነው።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችን ጨምሮ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ኢትዮጵያን በተለያዩ አገራት የወከሉ አምባሳደሮች፣ የፌዴራል እና የክልል መንግስት የስራ ኃላፊዎች በመድረኩ እየተሳተፉ ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ እየመጣ ያለው ሰላምና መረጋጋት በዲፕሎማሲ እና በኢኮኖሚ ልማት አበረታች ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የተገኘውን ሰላም በማጽናት ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና ልማት ምቹ ሁኔታን መፍጠር ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል።

አገራዊ የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥም በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በማረም ምቹ የልማት ምህዳርን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ በሚወጡ የግብርናና ሌሎች ምርቶች ሌሎች አገራት ተወዳዳሪ እስከመሆን መድረሳቸውን አንስተዋል።

በወጪ ንግድ ስርዓቱ ላይ በሚታየው ክፍተት የኢትዮጵያ አንጡራ ሀብቶች በህገ-ወጥ መንገድ ከአገር እየወጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ህገ-ወጥ ተግባር ሊቀለበስ እንደሚገባው ጠቁመዋል።

ኮንትሮባንድ እድገትን በማቀጨጭ የአገርን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማዛባት ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ገልጸዋል።

ለህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ተገቢውን መፍትሔ በመስጠት ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ የመንግስት አመራሮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።


 

በመድረኩም "ኢንቨስትመንቶች የሚያጋጥማቸው ተግዳሮቶች እና የመፍትሔ ሃሳቦች" እንዲሁም "የኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ ነባራዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ" በሚሉ ርዕስ ጉዳዮች ላይ በኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ ሌሊሴ ነሚ እና በጉምሩክ ኮሚሽነሩ ደበሌ ቃበታ የመነሻ ፅሑፍ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አገራዊ የቅንጅት መድረክ በ2003ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን መድረኩም በኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ለሚስተዋሉ ማነቆዎች መፍትሔ በማበጀት ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታን ለመፍጠር ያለመ ነው።

የመድረኩ ዝግጅት ዋና ዓላማ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በወጪ ንግድ እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ በቅንጅት ለመምራት በማሰብ እንደሆነም ተገልጿል።

መድረኩ አገራዊ የኢኮኖሚ ትብብር በማጠናከር የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም