የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የምክር ቤት አባላት በትኩረት መስራት አለባቸው ...የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ 

235

ሀዋሳ መጋቢት 11/2015 (ኢዜአ):-የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የምክር ቤት አባላት በትኩረት መስራት እንዳለባቸው የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሳሰቡ።

የሲዳማ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 2ኛ የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።

ጉባዔውን ሲጀምር አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ እንዳሉት የምክር ቤት አባላት የክልሉ መንግስት የያዛቸው ዕቅዶች በተገቢው መንገድ መተግበራቸውን መከታተል አለባቸው።

የምክር ቤቱ አባላት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር በመነጋገርና በመቀናጀት መሰራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

ከህዝብ ጋር በተደረገ ውይይት የተነሱ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዳሉ ያስታወሱት አፈ ጉባኤዋ፤ ለጥያቄዎቹ ተገቢው ምላሽ መሰጠቱን የምክር ቤቱ አባላት መከታተል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የምክር ቤቱ ጉባኤ በሁለት ቀናት ቆይታው ያለፉት ሰባት ወራት የመንግስት የስራ አፈጻጸም ይገመግማል፤ የተለያዩ አዋጆች ላይም በመወያየት ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም