ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ሀገራት በተደረጉ የአትሌቲክስ ውድድሮች አሸነፉ

604

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2015(ኢዜአ):- ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ ሀገራት በተደረጉ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ድል ቀንቷቸዋል።

በአሜሪካ ሎሳንጀለስ በተካሄደው የወንዶች ማራቶን አትሌት ጀማል ይመር በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት የማነ ጸጋዬ ደግሞ ሁለተኛ ሆኖ ጨርሷል።


 

በታይዋን ርዕሰ ከተማ ታይፔ በተደረገው የሴቶች ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያኑ በቀለች ጉደታ፣ መሰረት ድንቄ እና ገበያነሽ አየለ ከአንድኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ተከታትለው በመግባት አሸንፈዋል።

በቻይና ሸንዤን በተደረገ ማራቶን በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በቀዳሚነት አጠናቅቀዋል።


 

በዚህም በወንዶች አትሌት ባንታየሁ አዳነ በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ በሴቶች አገሬ ታምር በአንደኝነት ጨርሳለች።

በባርሴሎና በተደረገ የማራቶን ውድድርም ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዘይነባ ይመር ውድድሩን በአንደኝነት አጠናቃለች።

በአሜሪካ የኒዮርክ ግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ ደግሞ በሴቶች አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ ሁለተኛ ሆና ውድድሯን አጠናቃለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም