55ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የፋይናንስ፣የኢኮኖሚ ልማት እና ፕላን ሚኒስትሮች መደበኛ ስብስባ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
55ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የፋይናንስ፣የኢኮኖሚ ልማት እና ፕላን ሚኒስትሮች መደበኛ ስብስባ ተጀመረ

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2015 (ኢዜአ)፦ 55ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የፋይናንስ ፣የኢኮኖሚ ልማት እና ፕላን ሚኒስትሮች መደበኛ ስብስባ ዛሬ በሚኒስትሮች ደረጃ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ ።
ስብሰባው “የአፍሪካ መልሶ ማገገም እና ለውጥ በማፋጠን ኢፍትሐዊነትና ተጋላጭነትን መቀነስ” በሚል መሪ ቃል ነው የሚካሄደው።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የተገኙ ሲሆን፤የኮሚሽኑ አባል አገራት የፋይናንስ፣ እቅድ እና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች እና ተወካዮች ፣ የተመድ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የልማት አጋሮች ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
መደበኛ ስብሰባው ለሶስት ቀናት በባለሙያዎች ደረጃ ሲካሄድ ቆይቷል።
ባለሙያዎቹ በአፍሪካ ያለውን ድህነት እና ኢፍትሐዊነት እንዲሁም ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ቀጣናዊ ትስስር ላይ ያሉ ለውጦች ጨምሮ ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይም መክረዋል።
ሚኒስትሮቹ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ላለፉት ቀናት በተለያዩ አጀንዳዎች ተወያይተው ባቀረቡላቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሚኒስትሮች ስብሰባው ለሁለት ቀናት ይቆያል።