አካታችነትና ቅቡልነት ያለው ሀገረ-መንግሥት ለመገንባት ወጣቱን በማሳተፍ እየተሰራ ነው-የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ

ባህር ዳር መጋቢት 10/2015 (ኢዜአ)፦ አካታችነትና ቅቡልነት ያለው ሀገረ-መንግሥት በመገንባት የኢትዮጵያን ብልፅግና ዳር ለማድረስ ወጣቱን ያሳተፉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።


 

በባህር ዳር ከተማ ለብልፅግና ወጣቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት "በወጣቶች አቅም የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ይረጋገጣል" በሚል መሪ-ሃሳብ ለአንድ ሳምንት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።

የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ እንዳሉት ብልፅግና ሀገሪቱ ከነበረችበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የውጭ ግንኙነት ውድቀት በማውጣት በትክክለኛው መስመር እንድትጓዝ አድርጓል።

በኢኮኖሚው መስክ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና ማህበራዊም ሆነ ህዝባዊ ትስስርን በማጎልበት የሀገር ብልፅግናን እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

''አሁን የገጠመን ፈተና የእኔ ብቻ ትክክል፣ ሃቅና እውነት ነው ብሎ የሌላውን የማይቀበል ፅንፈኝነት ነው'' ያሉት አቶ አደም የወንድማማችነት መርህን ማስፈን የመሪ ድርጅቱ መርህ መሆኑን ወጣቶች ተገንዝበው መታገል እንደለባቸው አስገንዝበዋል።


 

''በሀገራችን በመደመር እሳቤ የተጀመረውን የትውልድ ግንባታ አጠናክሮ ለማስቀጠል ወጣቶች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው'' ያሉት ደግሞ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ መለስ ዓለሙ ናቸው።

"በአባቶቻችን ትግል አንድነቷ ፀንቶ የኖረችውን ሀገራችንን እስከነ ሙሉ ክብሯ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት ለመወጣት ስልጠናው አቅም እንደሆናችሁ እተማመናለሁ" ብለዋል።

ስልጠናው የተዘጋጀው ለቀጣይ ተልኳቸው እንቅስቃሴ አቅጣጫ የሚያመላክቱና የስራ መመሪያ የሚሆኑ ጉዳዮች ተመርጠው እንደሆነም ገልፀዋል።

እንዲሁም የወጣቶችን የእርስ በርስ ትስስር በማጎልበትና የብልፅግና መርሆዎችን በማስረፅ ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን በሚቻልበት ደረጃ በመሆኑ ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።

ለዚህም የወሰዱት ስልጠና ከዕውቀትና ክህሎት ባሻገር እርስ በርስ በመተዋወቅ፣ በመደጋገፍና በመረዳዳት የጋራ ዓላማ ግባቸውን ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።


 

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የብልፅግና ስራ አስፈጻሚ አባል ዶክተር ጌታቸው ጀንበር እንዳሉት በሀገራችን በልማትና በፖለቲካዊ ዘርፎች የመጡ ለውጦችን ዳር ለማድረስ የወጣቱ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

''አሁን ያለው የብልፅግና አመራር ቦታውን እየለቀቀ ሲሄድ የምትተኩት እናንተ ናችሁ'' ያሉት ዶክተር ጌታቸው ለዚህም በብልፅግና መርሆዎችና እሳቤዎች የወሰዳችሁት ስልጠና ለህይወታችሁ ስኬት ጠቃሚ ነው ብለዋል።

በተግባር እንቅስቃሴዎች መልካም ጉዳዮችን በማስፋትና ጉድለቶችን በማረም ከአዳዲስ እሳቤዎችና ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በማቀናጀት ሀገራዊ ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ የወጣቶች ሚና የላቀ መሆኑንም ገልፀዋል።


 

 

የብልፅግና ወጣቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወጣት አክሊሉ ታደሰ እንዳለው ስልጠናው በብልፅግና እሳቤዎችና ግቦች፣ በሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችና ዘመናዊ ኮሙኒኬሽን ላይ ያተኮረ ነው።

የሊጉ አመራሮችን ዕውቀትና ክህሎት በማጎልበት ለቀጣይ ተልዕኮ ከማዘጋጀት ባሻገር ለውጤታማ የስራ አፈፃፀም ስንቅ የሚሆን አቅም በመፍጠር አዳዲስ ስራዎችን ለመስራት መነሳሳት አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም