በሮም ማራቶን ለሻምበል አበበ ቢቂላ የመታሰቢያ መርሐ-ግብር ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በሮም ማራቶን ለሻምበል አበበ ቢቂላ የመታሰቢያ መርሐ-ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ መጋቢት 10 2015(ኢዜአ):- በሮም ማራቶን ለሻምበል አትሌት አበበ ቢቂላ የመታሰቢያ ዝግጅት ተከናውኗል።
የ2023 ሮም ማራቶን ዛሬ በጣሊያን ሮም ከተማ ተካሄዷል።
የተዘጋጀው መርሐ-ግብር እ.አ.አ በ1960 በሮም በተካሄደው 18ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ሻምበል አትሌት አበበ ቢቂላ በማራቶን በባዶ እግሩ በመሮጥ ለኢትዮጵያ ያስገኘውን የወርቅ ሜዳሊያ ለመዘከር በማሰብ መሆኑም ተጠቅሷል።
በዚህም አትሌቱን ለማሰብ የድንቅ ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ አየለ የሻምበል አትሌት አበበ ቢቂላ ከዛሬ 63 ዓመት በፊት በሮም በተካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር ማራቶን ላይ በባዶ እግሩ የሮጠውን በማሰብ የሮም ማራቶንን በባዶ እግር በመሮጥ የብዙዎችን ትኩረት ስበዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ በጣሊያን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሚቱ ሐምቢሳና በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰራተኞች፣ በሮም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የአትሌቱ ፎቶ ያረፈባቸውን ቲሸርቶች ለብሰው በመሮጥ አትሌቱን አስበውታል።
አምባሳደር ደምቱ በዝግጅቱ ለተሳተፉ ምስጋና ማቅረባቸውን በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያሳያል።
በ2023 የሮም ማራቶን በወንዶች ሞሮኳዊው አትሌት ታውፊክ አላም በሴቶች ኬንያዊቷ አትሌት ቤቲ ቼፕክዎኒ አሸንፈዋል።