ጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ ነው - ዶክተር ሊያ ታደሰ

1267

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2015 (ኢዜአ)፦ በማኅበረሰብ አቀፍ የጤና አጠባበቅ ዙሪያ የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ።

ሚኒስትሯ ይህንን ያሉት የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር 34ኛ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነው።


 

ማኅበሩ በአገሪቱ እየተከናወነ ላለው የጤና አገልግሎት ጥራት መሻሻል የጎላ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም በጤና ፖሊሲና ስትራቴጂ መሻሻል፣ የጤና ልማትና ተደራሽነት የተመለከቱ ግብዓት የሆኑ የምርምር ሥራዎች ላይ በሃላፊነት እየሰራ ነው ብለዋል።

መንግሥት ሁለተኛውን የጤና ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን አቅድ ለማሳካት የትኩረት አቅጣጫውን ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ላይ በትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው።

በዚህም ከአገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን በማግኘት የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻል ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ ያለው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በመሆኑም ማኅበሩ በሽታን በመከላከል ላይ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ በህክምና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ በትኩረት እንዲሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተለይም ማኅበሩ በስፋት የሚያከናወነውን ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና አጠባበቅ የምርምር ሥራዎች ተግባራዊ በማድረግ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

ጤና ሚኒስቴር ከዚህ አንጻር የሚሰራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚካሄደው የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር 34ኛ አመታዊ ጉባኤ የምርምር ውጤቶች ላይ ውይይት ማካሄድን ጨምሮ የእውቅናና የልምድ ልውውጥ መርሃ ግብሮችን አካቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም