በአግባቡና በጊዜው ግብርን መክፈል የታማኝ እጆች አሻራ ምልክት ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

212

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2015 (ኢዜአ) "በአግባቡና በጊዜው ግብርን መክፈል የታማኝ እጆች አሻራ ምልክት ነው" ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር "ግብር ለሀገር ክብር" በሚል መሪ ሳብ የታክስ ህግ ተገዥነት የንቅናቄ ማስጀመሪያና የእውቅና አሰጣጥ መርሃ-ግብር በሳይንስ ሙዚየም እያካሄደ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት መርሃ-ግብሩ የተዘጋጀው ታማኝ ግብር ከፋዮችን ለማበረታታትና አርዓያነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማስቻል ነው።

በተጨማሪም መርሃ-ግብሩ የተዘጋጀው የታማኝ ግብር ከፋዮችን አርዓያ በመመልከት ሌሎችም ወደ ግብር ሥርዓቱ እንዲገቡና የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ሃላፊነት እንዲወጡ ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ጠቁመዋል።

"በአግባቡና በጊዜው ግብርን መክፈል የታማኝ እጆች አሻራ ምልክትም ነው" ያሉት ከንቲባዋ ግብር የሚጠበቅበት የትኛውም አካል ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የከተማዋ መሰረተ ልማት ግንባታና የሕዝብ አገልግሎቶች የታመኝ ግብር ከፋዮች ውጤት መሆኑን ጠቁመው ይህም ግብር ከፋዩን ሊያስመሰግነው የሚገባ ተግባር መሆኑን አንስተዋል።  

አዲስ አበባ ከተማ ግብር የማመንጨት ከፍተኛ አቅም እንዳላት ጠቁመው አሁን ላይ የሚሰበሰበው ግብር ከዚህ አንጻር አነስተኛ መሆኑንና ይህም ሊያድግ እንደሚገባው አመላክተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በተለይም ሕገ-ወጥ ግብይትን በመከላከልና ዘመናዊ አሰራሮችን መዘርጋት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸው የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የፌዴራልና የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ ግብር ከፋዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም