የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በአቋም መለኪያ ጨዋታ የሩዋንዳ አቻውን 1 ለ 0 አሸነፈ

310

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ አቻው ጋር ያደረገው የአቋም መለኪያ ጨዋታን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተከናወነው ጨዋታ የአማካይ ተጫዋቹ ከነዓን ማርክነህ በ83ኛው ደቂቃ ላይ ለዋልያዎቹ የማሸነፊያዋን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።


 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እና ሌሎች የፌዴሬሽኑ አመራሮች እንዲሁም የእግር ኳስ ቤተሰቦች ጨዋታውን ተከታትለውታል።

ጨዋታው የተዘጋጀው ዋልያዎቹ ከጊኒ ጋር ላለባቸው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ አቋማቸውን እንዲፈትሹ መሆኑን ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

በኮትዲቭዋር አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ2023 በሚካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ከጊኒ ጋር በሞሮኮ ራባት መጋቢት 15 እና 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጨዋታዋን ታደርጋለች።


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጊኒ ጋር ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ከነገ በስቲያ ወደ ሞሮኮ ያቀናል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ አራት ከግብጽ ፣ ማላዊ እና ጊኒ ጋር የተደለደለች ሲሆን እስካሁን ሁለት ጨዋታ አድርጋ 3 ነጥብ በማግኘት በአንድ የግብ ክፍያ ምድቡን እየመራች ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም