ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገራት የኒዩክሌር ቴክኖሎጂዎችን በስፋትና በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ

487

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2015 ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገራት የኒዩክሌር ቴክኖሎጂዎችን በስፋትና በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ገለጸ።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የቴክኒካል ትብብር ኃላፊ ሁዋ ሊዩ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአፍሪካውያንን የቴክኖሎጂ ሽግግር ሂደት ለማሳካት በሰው ኃይልና በአቅም ግንባታ ድጋፍ ይደረጋል።

የአፍሪካ አገራት ኒዩክሌርን ለሰላማዊ አገልግሎቶች ለማዋል ያላቸውን መሻት ለማሳካት ኤጀንሲው በቅርበት አብሮ እንደሚሰራም ነው ያነሱት።

ምክትል ዋና ዳይሬክትሩ ሊዩየኢትዮጵያ መንግሥት የቁጥጥር ሥርዓቱን እንዲያጠናክር፣ በኒዩክሌር ሳይንስ፣ የኒዩክሌር ሃይል፣ ኒዩክሌርን ለህክምና ግብዓቶች የማዋል ሂደት ላይ ያለውን አቅም እንዲያሳድግ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎቱ አለንነው ያሉት።

ድጋፉም ኢትዮጵያዊ ተመራማሪዎችን በኒዩክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ማስተማርን እንደሚጨምር ተናግረዋል።

በኤጀንሲው የአፍሪካ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሻውካት አብዱልራዛቅ እንደገለጹት፤ በሀገራዊና አካባቢያዊ የምግብና የግብርና እንዲሁም የጤናና ስርዓተ ምግብ ፕሮጀክቶች ላይ ድጋፍ እያደረገ ነው።

የኒዩክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ በአፍሪካ ወደ ተግባር እየገባ ሲሆን 47 አገራትም ቴክኖሎጂውን ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ጥቅም ላይ እያዋሉ ነው።

ዳይሬክተሩ አያይዘውም የኒዩክሌር እውቀትን ማሳደግ፣ የውሃና የአካባቢ ደኅንነትን ማስተዳደር፣ የኒዩክሌር ሃይልና የጨረራ አጠቃቀምን በተመለከተም ለአፍሪካ ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት።

የኒዩክሌር ቴክኖሎጂ ከግብርና እስከ ህክምና ከውሃ ንፅህና እስከ ተባይ ቁጥጥር እንዲሁም ኤሌክትሪክ እስከማመንጨት የደረሰ ጥቅም አለው።

ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ቀጣናዊ ትብብርን በማሳደግ በኒዩክሌር ቴክኖሎጂ ራስን የመቻል ግብን ለማሳካት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።

ፕሮፌሰር ሻውካት አፍሪካውያን የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ የውሃ እጥረትንና የአፈር መከላትን ለማሻሻል እንዲሁም የእንስሳት ዘርፍ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የኒዩክሌር ቴክኖሎጂን መጠቀማቸው የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም