የብልፅግና ፓርቲ በፍትሃዊ ተጠቃሚነትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ላይ የተመሰረተ አንድነት ለማስፈን እየተጋ ነው--የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ

227

ባህር ዳር መጋቢት 10/2015 (ኢዜአ) ብልፅግና ፓርቲ በሀገራችን በፍትሃዊ ተጠቃሚነትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ላይ የተመሰረተ አንድነት ለማስፈን እየተጋ ያለ ፓርቲ ነው ሲሉ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

ለብልፅግና ወጣቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት "በወጣቶች አቅም የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ይረጋገጣል" በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ዳር ከተማ ለአንድ ሳምንት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል።

የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ፓርቲው በሀገሪቱ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና እኩል ተሳትፎን ማረጋገጥ ዋናው ተግባሩ ነው።


 

ይህም በየአካባቢው ህዝቡ ባለው ፀጋና አቅም ልክ ሰርቶ የሚበለፅግበት ሀገር ለመገንባት በር የከፈተ በመሆኑ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካው መስክ ስኬት መመዝገቡን ተናግረዋል።

በምርት አይነት ብዝሃነትን ያካተተ የኢኮኖሚ ፓሊሲ በመከተል ዘላቂነት ያለው ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የብልፅግና ወጣቶች ሊግ አመራሮችና አባላት የበኩላቸውን እንዲውጡም አሳስበዋል።


 

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀንበር በበኩላቸው የብልፅግና ወጣቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አሁን የሚስተዋለውን ፅንፈኝነትን በመታገልና ህብረ-ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር ሀገር ለማፅናት የተያዘውን ግብ ለማሳካት ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።

አክለውም አሁን ላይ የብሄር፣ የፖለቲካና የሃይማኖት ፅንፈኝነት ችግር የብልፅግና ፓርቲያችን ፈተና በመሆን የተግባር ስራዎቻችን ላይ ጥላ በማጥላት ላይ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።

በህብረ-ብሄራዊ አንድነት የተመሰረተው ብልፅግና በእሳቤና በተግባር እንከን የሌለው ቢሆንም፤  የውስጥና የውጭ ፅንፈኞች ችግር ሲፈጥሩበት የሚስተዋል በመሆኑ ወጣቱ ይህን ተገንዝቦ፤ ለለውጡ ቀጣይነት መስራት አለበት ብለዋል።

በኢትዮጵያ ተራማጅ አስተሳሰብና ለውጥን ለማረጋገጥ የሚታገል ወጣት በየደረጃው ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን የገለፀው ደግሞ የብልፅግና ወጣቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወጣት አክሊሉ ታደሰ ነው።

ፕሬዝዳንቱ እንዳለው የተጀመርውን ሀገራዊ ግንባታ ግብ ለማሳካት በየደረጃው የሚገኘውን የሊጉ አመራርና አባላት አቅም በማጎልበትና በስነ-ምግባር የማነፅ ስራ ተጀምሯል።


 

ለማዕከላዊ አባላቱ ሰሞኑን በብልፅግና መርሆዎች፣ እሳቤዎችና ግቦች ላይ ያተኮረ ስልጠና መስጠት መቻሉ ዋና ማሳያ ነው ብሏል።

ይህም ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዊውን በመገንዘብ በሀገር ደረጃ እየገጠሙን ያሉትን ተግዳሮቶች ለማለፍ የሚያስችል አቅም ለመገንባት መሆኑን ተናግሯል።

በተጨማሪም የሊጉ አመራሮችና አባላት ተራማጅ አስተሳሰብንና አመለካከትን አጠናክሮ በማስቀጠል የተጀመረውን ለውጥ ዳር የማድረስ ኃላፊነትን ለመወጣት በማለም ነው ብሏል።

የስልጠናው ተሳታፊዎችም ያገኙትን እውቀትና ልምድ በመጠቀም የነገ ሀገር ተረካቢ መሪ መሆናችሁን ተገንዝባችሁ መዘጋጀት አለባችሁ ሲል መልዕክት አስተላልፏል።

በባህርዳር ከተማ ለስምንት ተከታታይ ቀናት በተሰጠው ስልጠና 223 የብልፅግና ወጣቶች ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መሳተፋቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም