የሴኡል ማራቶንን አትሌት አምደወርቅ ዋለልኝ አሸነፈ

371

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2015 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኮሪያ በተካሄደው የሴኡል ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት አምደወርቅ ዋለልኝ አሸነፈ።

የሴኡል ማራቶን ረጅም እድሜ ካስቆጠሩ ውድድሮች አንዱ ሲሆን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1931 የተጀመረ ነው።

ትናንት ምሽት 77ኛው የሴኡል ማራቶን ውድድር ተካሂዷል።

በውድድሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል።

በ2014ዓ.ም መስከረም ወር ላይ በተካሄደው የኮፐንሀገን የግማሽ ማራቶን ውድድርና በ2013ዓ.ም በህንድ ኤርቴል ግማሽ ማራቶን አሸናፊ የነበረው አትሌት አምደወርቅ ዋለልኝ የሴኡል ማራቶንን አሸንፏል።


 

አትሌት አምደወርቅ ውድድሩን ለመጨረስ 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ26 ሴኮንድ ወስዶበታል።

ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሽፈራ ታምሩ ደግሞ 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ38 ሴኮንድ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ጨርሷል።

አትሌት ሃፍቱ አሰፋ ደግሞ 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ48 ሴኮንድ ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።

ባለፈው ዓመት በተካሄደው 76ኛው የሴኡል ሶውል የወንዶች ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሞስነት ገረመው አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም