የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ አቻው ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ዛሬ ያከናውናል

463

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ አቻው ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታውን ዛሬ ያከናውናል።

የአቋም መለኪያ ጨዋታው ዋልያዎቹ ከጊኒ ጋር ለሚያደርጉት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ  አቋማቸውን እንዲፈትሹ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል።

ጨዋታው በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ይደረጋል።


 

43 አባላት ያሉት የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ልዑክ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ጨዋታውን ለማድረግ ትናንት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን የመጀመሪያ ልምምዳቸውንም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ አከናውነዋል።

በኮትዲቯር አስተናጋጅነት .. 2023 በሚካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ከጊኒ ጋር በሞሮኮ ራባት መጋቢት 15 እና 18 ቀን 2015. ጨዋታዋን ታደርጋለች።


 

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ 23 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ተጫዋቾቹ ዝግጅታቸውን ከጀመሩ ዛሬ አምስተኛ ቀን አስቆጥረዋል።

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ ለደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሳንዳውንስ ክለብ የሚጫወተው አቡበከር ናስር ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ማገገም ባለመቻሉ ከብሔራዊ ቡድኑ  ስብስብ ውጪ የሆነ ሲሆን በምትኩ የኢትዮጵያ መድን አጥቂ ኪቲካ ጀማ ተተክቷል።


 

በተያያዘም ሌላኛው የብሔራዊ ቡድኑ አጥቂ ይገዙ ቦጋለ በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጪ ሆኗል።

የሲዳማ ቡናው ተጫዋች ከጉዳቱ ለማገገም የአራት ሳምንት እረፍት እንደሚያስፈልገው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ብሔራዊ ቡድኑ ከሩዋንዳ ጨዋታ በፊት የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ አድርጓል።


 

ዋልያዎቹ ከጊኒ ጋር ላለባቸው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ከነገ በስቲያ ወደ ሞሮኮ ያቀናሉ።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ አራት ከግብጽ፣ ማላዊ እና ጊኒ ጋር የተደለደለች ሲሆን እስካሁን ሁለት ጨዋታ አድርጋ 3 ነጥብ በማግኘት በአንድ የግብ ክፍያ ምድቡን እየመራች ትገኛለች

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም