የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ትውልድ ያለፈበትን መንገድ የሚያሳይና ነገን የተሻለ ለማድረግ መፍትሄ የሚያመላክት ነው...በመጽሐፉ ላይ ሂስ ያቀረቡ ባለሙያዎች 

1267

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2015 (ኢዜአ ) የመደመር ትውልድ መጽሐፍ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትውልድ ያለፈበትን መንገድ የሚያሳይና ነገን የተሻለ ለማድረግ መፍትሄ የሚያመላክት መሆኑን በመጽሐፉ ላይ  ሂስ ያቀረቡ ባለሙያዎች ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተጻፈው የመደመር ትውልድ መጽሐፍ የክልል ርእሳነ መስተዳደሮችን ጨምሮ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ተመርቋል፡፡

በሶስት ክፍሎችና በ10 ምዕራፎች የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍ የትውልድ ምንነት አፈጣጠርና አካሄድ ምን እንደሚመስል ያስቃኛል፡፡

መጽሐፉ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ትውልዶችን ወግ አጥባቂ፣ ህልመኛ፣ ተስፈኛ፣ ውል አልባ እና የመደመር ትውልዶች ሲል በአምስት የሚከፍላቸው ሲሆን፤ በአማርኛ፣ አፋን ኦሮሞና እንግሊዘኛ ታትሞ ለንባብ በቅቷል፡፡

ከመጸሐፉ የሚገኘው ገቢም በሁሉም ክልሎች ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቅርሶችን ለማደስ እንዲሁም በአንዳንድ ክልሎች ደግሞ ቤተ መጽሃፍት ለመገንባት እንደሚውል ተጠቁሟል፡፡

መጽሃፉን በሚመለከት ሂሳዊ ዳሰሳ ካቀረቡት መካከል አንጋፋው የኪነጥበብ ባለሙያ ደበበ እሸቱ ደራሲው ወግ አጥባቂ ትውልድ በሚል ያስቀመጡትን ሃሳብ ዳሰዋል፡፡

ደራሲው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ይህን ትውልድ በዓድዋ ድል ኩራትና ሁለተኛው የጣሊያን ጦርነት ቁርኝት የተፈጠረ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡

ወግን በመጠበቅ ዘመናዊነትን ሊያሳልጥ የተነሳ መሆኑንና የራሱ ድክመት ቢኖርበትም በመልካምነት የሚነሱና አገር ያቆዩ አሻራዎችን እንዳስቀመጡ በማንሳት፡፡


 

ደራሲ ህይወት ተፈራ በበኩሏ በመጽሐፉ ላይ ህልመኛው ትውልድ በሚል የተቀመጠውን ሃሳብ ዳሰዋል፡፡

ይህ ትውልድ አብዮታዊ ንቅናቄዎች በበዛበት ወቅት ያለፈ ትውልድ ሲሆን፤ የጠላትነት ፖለቲካን በስፋት በማራመድ በትውልዶች መካከል የፓራዳይም ልዩነት ማምጣቱን ያነሳሉ፡፡

ደራሲው ይህን ትውልድ አገራዊ ችግሮችን ከውጭ በመጡ መፍትሄዎች ለመፍታት ረዥም ርቀት የተጓዘ መሆኑን በግልጽ ማስቀመጣቸውን አንስተዋል፡፡

በ1990ዎቹ መጀመሪያ የተፈጠረውንና መጽሐፉ "ውል አልባ ትውልድ"  ሲል ያሰቀመጠው ሃሳብ ላይ ዳሰሳ ያቀረቡት ዶክተር ታምራት ኃይሌ፤  ይህ ትውልድ በቀይ እና ነጭ ሽብር ዘመን ጀምሮ በነበረው የፖለቲካ እቀባ ምክንያት ከፖለቲካ አውድ የመራቅ አዝማሚያ የሚያሳይ መሆኑን ደራሲው በግልጽ ማመላከታቸውን ይናገራሉ፡፡



 

በ1997 በተወሰነ መልኩ በፓለቲካው አውድ ውስጥ ለመሳተፍ ቢሞክርም ከዚያ በኋላ በተፈጠረው የፖለቲካ አካሄድ ምክንያት ተመልሶ ወደነበረበት መመለሱን ጠቅሰዋል፡፡

መጽሐፉ ፈጥነው ለማንበብ የሚያጓጓ ግን ደግሞ በየ መሃሉ ለማሰላሰል ጊዜ የሚፈልግ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የመደመር ትውልድ መጽሃፍ በትውልድ ጉዞ ውስጥ ትናንትና እና ዛሬን በማሳየት ነገ ምን ሊመስል እንደሚችል አሻግሮ የሚጠቁም መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ዶክተር ዮሴፍ ቤኮ ናቸው፡፡


 

መጽሃፉ የአሁኑ ትውልድ ወደ ኋላ ተመልሶ ራሱን በቀደመው ትውልድ መስታዎት እንዲመለከት እድል እንደሚፈጥርም እንዲሁ፡፡

በመጽሃፉ ላይ ጥቅል ሂስ ያቀረቡት ዶክተር መሃመድ ሁሴን፤ የመደመር ትውልድ መጽሃፍ ደራሲው በተመሳሳይ አውድ ከዚህ ቀደም ለንባብ ካበቋቸው መደመርና የመደመር ትውልድ መጽሃፍ እንደሚለዩ ተናግረዋል፡፡


 

የቀደሙት መጽሃፍት የአገሪቱን ፖለቲካና ታሪክ እንዲሁም የህብረተሰቡን የወደፊት አቅጣጫ የሚያመላክቱ ሲሆኑ፤ የአሁኑ መጽሃፍ ግን ትውልዱን በምናባዊ ተሰጥኦና እውቀት ኮትኩቶ ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረጉን አንስተዋል፡፡

ይህም ትውልዱ ራሱን ፈትሾ እንዲያይ በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም