አገር አቀፍ ከ20 ዓመት በታች የቼዝ ሻምፒዮና በያዝነው መጋቢት ወር ይካሄዳል

520

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2015(ኢዜአ):- አገር አቀፍ ከ20 ዓመት በታች የግል የበላይነት ቼዝ ሻምፒዮና በያዝነው መጋቢት ወር በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ቼዝ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ለስድስተኛ ጊዜ የሚዘጋጀው አገር አቀፍ ከ20 ዓመት በታች የግል የበላይነት ቼዝ ሻምፒዮና ከመጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

በዚህ ለሁሉም ክፍት በሆነው ሻምፒዮና የሚካፈሉ ስፖርተኞች ምዝገባ እየተካሄደ ሲሆን እስከ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም የሚቆይ እንደሆነ ነው የተገለጸው።

በሻምፒዮናው አሸናፊ የሚሆኑት ኢትዮጵያን ወክለው ሱዳን በሚካሄደው የግል የበላይነት ሻምፒዮና/ የዞን 4 ነጥብ 4  ውድድር / ይመረጣሉ። 

በዚህ የግል የበላይነት ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታ እስከ አሥር የሚደርሱ ስፖርተኞችን ማሳተፍ እንደምትችል ነው የተነገረው።

እንዲሁም በመላው አፍሪካ ጨዋታ የሚሳተፉ ዕጩዎችን ለመምረጥ እንደሚያግዝ ነው ፌዴሬሽኑ ያስታወቀው።

ይህ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ከመጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄድ ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም