የአሁኑ የመደመር ትውልድ ችግሮች የማያቆሙት ፤ ሀገር የማሻገር አቅምና እድል ያለው ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ - ኢዜአ አማርኛ
የአሁኑ የመደመር ትውልድ ችግሮች የማያቆሙት ፤ ሀገር የማሻገር አቅምና እድል ያለው ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ መጋቢት 9/2015(ኢዜአ):- የአሁኑ የመደመር ትውልድ ችግሮች የማያቆሙት ፤ ሀገር የማሻገር አቅምና እድል ያለው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ክልሎች መጽሐፉን ሽጠው የሚያገኙትን ገቢ ሙሉ ለሙሉ ለመዝናኛ ቦታዎች ግንባታና ለቅርሶች እድሳት እንዲያውሉት ተብርክቶላቸዋል፡፡
በአማርኛ፣ በኦሮምኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀው 'የመደመር ትውልድ' ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የጻፉት ሶስተኛ መፅሐፍ በዛሬው እለት ተመርቆ ለንባብ በቅቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ የመደመር ትውልድ መጽሐፍ የትውልድን ግንባታ አሰናስሎ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
በመደመር ሀሳብ ላይ የሚያጠነጥን፣ የመደመር መንገድ በጉዞ የሚገለጥ እንዲሁም የመደመር ትውልድ የትውልድ ግንባታን የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
"የመደመር ትውልድ" መጽሐፍ ትውልዱን "ወግ አጥባቂ፣ ህልመኛ፣ ውል አልባ፣ ባይተዋርና የመደመር ትውልድ" ሲል በአምስት ይከፍላቸዋል፡፡
ከእነዚህ መካከል የመደመር ትውልድ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና በማሸጋገር ትልቅነቷን እንደሚያረጋግጥ እምነት የሚጣልበት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ያለፈውን ማስተካከል፣ የዛሬውን ማስፋፋትና ፈተናዎችን ተሻግሮ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ነገን ማበርከት የመደመር ትውልድ ኃላፊነት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የመደመር ትውልድ መቅረጽ ያስፈለገውም ፈተና ስላለ ነው ብለዋል፡፡
የመደመር ትውልድ በአቧራ የማይናወጥ ብቻ ሳይሆን አሻራ በማስቀመጥ ለቀጣዩ ትውልድ ከእዳ ይልቅ እድል መፍጠር የሚችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ፈተናዎችን ተጋፍጦ በማለፍ የትናንት እና የነገውን ትውልድ ማገናኘት እንጂ ተስፋ ቆርጦ መቆም የመደመር ትውልድ ባህርይ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሁነትን በጊዜው በመከተብ ታሪክን ለትውልድ ማስቀመጥን ያለመ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
በቀጣይም የፖለቲካ ገበያውንና ያለፉትን ሁለት ዓመታት ጦርነት በተመለከተ ሌላ መጽሐፍ ለማበርከት እቅድ እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የመደመር ትውልድ መጽሐፍ በሀሳብም በገንዘብም ትውልድ የሚሰራ በመሆኑ ገቢው ክልሎች ከመጽሐፉ ሽያጭ ያገኙትን ገንዘብ የመዝናኛ ስፍራዎችን ለመገንባትና ቅርሶችን ለማደስ እንዲጠቀሙበትም በስጦታ አበርክተዋል፡፡