ኢትዮጵያ የቱሪዝም ኃብቷን በማልማት ለመጠቀም ለምታደርገው ጥረት ድጋፍ እናደርጋለን- የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የቱሪዝም ኃብቷን በማልማት ለመጠቀም ለምታደርገው ጥረት ድጋፍ እናደርጋለን- የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን
አዲስ አበባ መጋቢት 09/2015 (ኢዜአ) የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብቷን በማልማት ለመጠቀም ለምታደርገው ጥረት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገለጸ።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ዶክተር ማማ ኬታ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም ሀብትና ትልቅ የመልማት አቅም ያላት አገር መሆኗን ገልጸዋል።
በምስራቅ አፍሪካ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ ንግድና ምጣኔ ሀብት ትስስርን ለማፋጠንም ወሳኝ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ልማት እድገት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብቷን በማልማት ከዘርፉ ለመጠቀም ለምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የቴክኒክና ሌሎችም አስፈላጊ ድጋፎችን ያደርጋል ሲሉ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብት ዘርፈ-ብዙ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ማማ፤ የመልክዓ-ምድሯ አቀማመጥ፣ ታሪክና ቅርሷ፣ የአየር ንብረቷ፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ጸጋዎቿ ትልቅ ሀብቶች ናቸው ብለዋል።
በዘርፉ ልማት አገሪቱ እያከናወነች ያለውን የመረጃ አያያዝና የቱሪዝም ልማት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የሚያደርገውን ድጋፍ ይቀጥላል ብለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ አገራት ከድህነት ለመውጣት የሚቀርጿቸው ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በዋናነት የቱሪዝም ዘርፉን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበትም መክረዋል።
የማዕድን፣ ግብርና እንዲሁም ሌሎች ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ሴክተሮች ከድህነት የመውጫ አማራጮች ስለመሆናቸውም አብራርተዋል።
በቀጣናው የንግድ፣ የመሰረተ-ልማትና ሌሎች ትስስሮችን ማጠናከርም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ተግባራዊ ሲሆን ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከድህነት ለመውጣት ዓይነተኛ ሚና እንዳለውም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።