በአማራ ክልል  ዘንድሮ 316 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ  መከናወኑን  የግብርና ቢሮ አስታወቀ 

617

ባህር ዳር፤  መጋቢት  9 /2015 ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማጠናከር  በዘንድሮው የበጋ ወራት  316 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

 ስራው የተከናወነው  በስምንት ሺህ 585 ተፋሰሶች  ውስጥ መሆኑን ቢሮው ገልጿል።

በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመላለም ምህረት ለኢዜአ እንዳመለከቱት፤ ከጥር ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ከተከናወነው ስራ  በ311 ሺህ 263 ሄክታር መሬት ላይ የማሳና የጋራ እርከን ይገኝበታል። 

እንዲሁም አራት ሺህ 813 ሄክታር የቦረቦር ልማትና አራት ሚሊዮን 893 ሺህ አነስተኛ የውሃ ማስረጊያ "ስትራክቸሮች" መሰራታቸውንም ገልጸዋል።

በተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራው ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በመሳተፍ በበጋ ወራ ለማከናወን የተያዘውን እቅድ ሙሉ በሙሉ ማሳካት መቻሉን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

የተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ 7ሺህ 100 የተፋሰስ ልማት ህብረት ስራ ማህበራት ለማቋቋም ታቅዶ 2ሺህ 284 በማቋቋም ህጋዊ እውቅና አግኝተው ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል።

ቀሪዎቹን ማህበራት እስከ መጪው ግንቦት ወር መጨረሻ አቋቁሞ ለማጠናቀቅ የሚያስችል የተጠናከረ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

የተፋሰስ ልማት ህብረት ስራ ማህበራቱም ተፋሰሶቹ በዘላቂነት ተጠብቀው ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ከማድረግ ባለፈ ዋነኛ የእንስሳት መኖ መገኛ ምንጭ እንዲሆኑ እንደሚያደርጉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ የጋፍቲ ጉንካን ቀበሌ አርሶ አደር አንማው ጋሻዬ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፉት 12 ዓመታት ባከናወኑት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራም የአፈር መሸርሸር እየቀነሰ እንዲመጣ ማስቻሉን ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ  ከመጀመራችን በፊት መሬቱ ለምነቱን ከማጣቱ የተነሳ በሄክታር እስከ 8 ኩንታል እናገኝ የነበረው ምርት አሁን እስከ 15 ኩንታል እንድናገኝ አስችሎናል ብለዋል። 

በዚሁ ዞን  ደንበጫ ወረዳ የእግዚአብሄር አብ ቀበሌ  አርሶ አደር አብራራው ፈንቴ ፤  የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ጠንክረን መስራታችን የመሬቱ የአፈር ለምነት እየጨመረ እንዲመጣ አድርጓል ሲሉ ገልጸዋል።  

በቀጣይም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ያለማንም ቀስቃሽ አጠናክረው  እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት በአርሶ አደሩ ተሳትፎ 295 ሺህ 364 ሄክታር መሬት ላይ የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ መከናወኑ ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም