በ 'ጅቡቲ ኢንተርናሽናል ሚት' የአትሌቲክስ  ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል ቀናቸው

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2015(ኢዜአ):-  ለስድስተኛ ጊዜ በተካሄደው 'ጅቡቲ ኢንተርናሽናል ሚት' የአትሌቲክስ  ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች ድል ቀንቷቸዋል።

በ5 ሺህ ሜትር ሴቶች አለሽኝ ባወቀ 16 ደቂቃ ከ15 ሰከንድ ከ30 ማይክሮ ሴኮንድ በሆነ ሰዓት በቀዳሚነት አጠናቃለች።

እንዲሁም አዳኔ አንማው 16 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ ከ66 ማይክሮ ሴኮንድ ውድድሩን በሁለተኝነት ጨርሳለች።

በሴቶች 1 ሺህ 500 ሜትር በተካሄደ ውድድር አትሌት ነጻነት ደስታ 4 ደቂቃ ከ8 ሴኮንድ ከ58 ማይክሮ ሰከንድ በቀዳሚነት አጠናቃለች።

ሌላኛዋ ፍሬዘውድ ተስፋዬ 4 ደቂቃ ከዘጠኝ ሰኮንድ ከ43 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት ውድድሩን ሁለተኛ ሆና ጨርሳለች።

በወንዶች 1 ሺህ 500 ሜትር በተካሄደ ውድድርም አትሌት አብዱልከሪም ተኬ 3 ደቂቃ 8 ሰከንድ ከ16 ማይክሮ ሰከንድ በቀዳሚነት አጠናቋል።

በተጨማሪም በወንዶች 800 ሜትር ኤፍሬም መኮንን ቀዳሚ ሆኖ ሲጨርስ በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች ደግሞ አትሌት ዘነበ አየለ ሁለተኛ ወጥቷል።

በ'ጅቡቲ ኢንተርናሽናል ሚት'  የአትሌቲክስ ውድድር ከኢትዮጵያ አትሌቶች በተጨማሪ የጅቡቲ ፣ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ብሩንዲ፣ሶማሊያ፣ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ሴኔጋል እና ካሜሮን  አትሌቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም