ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ እንዲያድግ የመንግስት ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ 


አዲስ አበባ መጋቢት 9/2015(ኢዜአ):-መንግስት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ እንዲያድግ የሚያደርገውን ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ። 

አየር መንገዱ በአሁኑ ሰአት ከ13 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የበረራ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።


የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና አመራሮች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለደንበኞቹ የሚሰጠውን የበረራ አገልግሎት በተመለከተ ምክር ቤቱ አየር መንገዱ ላሉበት ተግዳሮቶች የመፍትሔ አካል መሆንን አላማ ያደረገ ጉብኝት አድርገዋል።


የተቋሙንም የተለያዩ የስራ ክፍሎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።


 


የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ተመራጭ፣ ግዙፍ እና ግንባር ቀደም ተቋም ነው” ብለዋል።


አየር መንገዱ በበረራ አገልግሎቱ ውጤታማ እንዲሆን መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።


የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው አየር መንገዱ በ77 ዓመታት ታሪኩ በእድገት ግስጋሴ ውስጥ እንደሚገኝና አሁን ላይ ከ13 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የበረራ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።


አየር መንገዱ 141 አውሮፕላኖች ሲኖሩት በ131 አገራት የበረራ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል። 


ከነዚህም ውስጥ 126ቱ አውሮፕላኖች የሕዝብ ማጓጓዣ፤ የተቀሩት 15 ደግሞ የካርጎ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ነው አቶ መስፍን ያስረዱት።


አየር መንገዱ የለውጥ ስትራቴጂ ግቦችን በማዘጋጀት እ.አ.አ እስከ 2030 ድረስ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር ከ141 ወደ 200፣ የተጓዦችን ቁጥር ደግሞ ከ13 ሚሊዮን ወደ 65 ሚሊዮን ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


ተቋሙ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ተሰማርቶ እየሰራ እንደሚገኝ እና ለዜጎች የተለያዩ የበጎ አድራጎት ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።


የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ መጨመር፣ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ፣ የአውሮፕላን ጥገና መለዋወጫ እቃዎች ዋጋ መናር፣ የሰራተኛ ፍልሰት እና የመሬት ካሳ ክፍያ አየር መንገዱ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አመልክተዋል።


ችግሮቹን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የምክር ቤቱ ድጋፍ ወሳኝ እንደሆነ ዋና ስራ አስፈጻሚው መግለጻቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም