የጤና ባለሙያዎች ብቃት ጥራት ላለው የጤና አገልግሎት ቁልፍ ሚና ይጫወታል - ዶክተር ሊያ ታደሰ - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ባለሙያዎች ብቃት ጥራት ላለው የጤና አገልግሎት ቁልፍ ሚና ይጫወታል - ዶክተር ሊያ ታደሰ
አዲስ አበባ መጋቢት 9/2015 (ኢዜአ)፦ የጤና ባለሙያዎች ብቃትና ተነሳሽነት ጥራት ላለው የጤና አገልግሎት ወሳኝ አበርክቶ እንዳለው የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር 59ኛ ዓመታዊ ጉባኤ እና ዓለም አቀፍ የጤና አውደ ርዕይ በማካሄድ ላይ ነው።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ለጤናው ስርዓት “በርካታ” አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስቴርም በአገር ደረጃ ያለውን የጤና ስርዓት ለማጎልበት የተለያዩ ስትራቴጂዎች በመቅረጽ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የጤና አገልግሎት ጥራትና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥና መረጃን መሰረት ያደረገ የሕክምና አገልግሎትን ለመስጠት የአመራርና የጤና ፋይናንስ ስርዓትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
እንዲሁም የጤናው ዘርፍ ሰራተኞች ተነሳሽነት ያላቸው ብቁና ሙያዊ ስነ ምግባር የተላበሱ እንዲሆኑ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው ዶክተር ሊያ ያብራሩት።
በዚህ ረገድም የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር የተለያዩ ኮርሶችን በማዘጋጀት፣ ተደራሽነትን በማሻሻል፣ በብቃት ማረጋገጥ እና በስልጠና አቅራቢነት እየሰራ ያለውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በመንግስትም ሆነ በግል ጤና ተቋማት የሕክምና ቴክኖሎጂዎችን ማዘመን እንደሚገባና ለዚህም የሙያ ማህበራት፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችና የሚዲያ ተቋማት በተቀናጀ መንገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ ዶክተር ሊያ ማሳሰባቸውን ከጤና ሚኒስቴር ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡