መንግስት በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር አመካኝነት ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሃብቷ ተጠቃሚ እንድትሆን በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው...የግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር አመካኝነት ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሃብቷ ተጠቃሚ እንድትሆን በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው...የግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ መጋቢት 8/ 2015 (ኢዜአ)፦መንግስት በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር አመካኝነት ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሃብቷ ተጠቃሚ እንድትሆን በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ተናገሩ፡፡
የእርድ እንስሳት አቅርቦትን ማሻሻል ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል የዘርፉ ስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በመድረኩም በእርድ እንስሳት ላይ ያለው የገበያ ትስስር እጥረትና የጥራት መጓደል ኢትዮጵያ ከዘርፉ እንዳትጠቀም እንዳደረጋት ተጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ የእርድ እንስሳት አቅራቢዎች ማህበር ስራ አስኪያጅ መኮንን ጋሹ በተለይ የእርድ እንስሳት ዝርያን ማሻሻል ላይ ትኩረት በመስጠት የጥራት መጓደሉን ለመቅረፍ መስራት እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ስጋ አምራች ላኪዎች ማህበር ዋና ፀሀፊ አበባው መኮንን በበኩላቸው በእርድ እንስሳት አምራችና በተጠቃሚው መካከል ያለው የገበያ ትስስር በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም የቁም እንስሳት ግብይቱ ለኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ እንዲጋለጥ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ችግሩን በመፍታት ረገድ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ዘርፉ ገበያ ተኮር ባለመሆኑ እና ባለመዘመኑ በሚፈለገው ልክ ገቢ አለማምጣቱን የተናገሩት ደግሞ በእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት የሶሺዮ ኢኮኖሚ እሴት ሰንሰለት አስተዳደር ምርምር ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ሳህሉ ሙሉ ናቸው፡፡
በመሆኑም መንግስት በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር አማካኝነት ችግሩን ለመፍታት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ መንግስት የእንስሳት ሃብትን ከሌሎች የውጭ ንግድ መስኮች ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
በዋናነት የእንስሳት ሃብትን ጥቅም ላይ ለማዋል ገቢራዊ የሆነው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በዚህ ረገድ አብነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አመራሩ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ ለስንዴ ልማትና ሌሎች አገራዊ መርሃ ግብሮች ላይ ያሳየውን ቁርጠኝነት በሌማት መርሃ ግብር ለመድገም እየሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
በመሆኑም ለመርሃ ግብሩ ስኬት በጋራ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
በእንስሳት ተዋጽኦ ወጪ ንግድ ለመሰማራት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ ያልገቡ ድርጅቶች በአግባቡ ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸው ገልጸው፤ ይህን በማያደርጉት ላይ ግን እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት የእንስሳት ምርትና ውጤቶችን ወደ ውጭ በመላክ በአጠቃላይ 1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ አግኝታለች።
ሀገሪቷ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት 2 ሚሊዮን ቶን የእንስሳት ምርትና ተዋጽኦን አቀነባብሮ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ7 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ማቀዷን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።