በጋምቤላ ክልል አምስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ ልማት 12  ሚሊዮን የሚጠጉ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው - የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ

576

 ጋምቤላ  መጋቢት 8/2015 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል በአምስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ ልማት 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ባለፈው የክረምት ወቅት ከተተከሉት 10 ሚሊዮን ችግኞች መካከል "85 መቶ የሚሆነው መጽደቁን"  ገልጿል።

የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ አጃክ ኡቻላ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ የአካባቢ ልማትና ጥበቃ ሥራዎችን በማጠናከር ምርታማነትን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።

በተያዘው የበጋ ወራትም ከ60 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ የተራቆተና የእርሻ መሬት ላይ ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በበጋው ወራት የአፈርና ውሃ ጥበቃ እና ልማት የተካሄደባቸው አካባቢዎችን በአምስተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሐግብር በችግኝ ለማልበስ ታቅዷል ብለዋል።

አካባቢዎቹን በስነ-ህይወታዊ ዘዴ ለማልበስም በክልሉ በሚገኙ 104 የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች 11 ነጥብ 75 ሚሊዮን ችግኞችን የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው አቶ አጃክ የጠቆሙት።

ችግኞቹ የፍራፍሬ እና የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውንም በመግለጽ።

በተያያዘም "በክልሉ ባለፈው የክረምት ወቅት ከተተከሉት 10 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መካከል 85 በመቶ የሚሆነው ጸድቋል" ነው ያሉት የቢሮ ኃላፊው። 

የጋምቤላ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ባለሙያ አቶ ቻም ኡራሚ በበኩላቸው፣ በ2014 የክረምት ወቅት ሕብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወነ የእንክብካቤ ስራ በአንዳንድ አካባቢዎች ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጀ ችግኞቹ መጽደቀቻውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የበጋውን ሞቃታማ የአየር ጸባይ ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የሰደድ እሳት ለመከላከል በተከናወኑት የሰደድ እሳት መከላከያ እርከን ስራዎችም ይደረስ የነበረን ቃጠሎ መቀነስ መቻሉን አመልክተዋል።

በጋምቤላ ከተማ በከተማ ግብርና ሥራ ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል ወጣት ሙኒር ኢሳ በሰጠው አስተያየት፣ አሁን ላይ ከግብርና ልማት በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሚታ ያላቸውን ችግኞች በማልማትና በመትከል ተጠቃሚ መሆን መጀመሩን ገልጿል።

በተለይ ከጓሮ አትክልት በተጨማሪ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ ሎሚ፣ ብርቱካንና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሚታ ያላቸውን ችግኞች በማልማት በምግብ እራስን ለመቻል እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም