የቅመማ ቅመም ምርት ግብይት የሚያቀላጥፉ አሰራሮችን በመዘርጋት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ ነው-ቡናና ሻይ ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የቅመማ ቅመም ምርት ግብይት የሚያቀላጥፉ አሰራሮችን በመዘርጋት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ ነው-ቡናና ሻይ ባለሥልጣን
አዲስ አበባ መጋቢት 8/ 2015 (ኢዜአ)፦ የቅመማ ቅመም ምርት ግብይት የሚያቀላጥፉ አሰራሮችን በመዘርጋት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ኢትዮ-አግሮ የመስኖ ስንዴና ቅመማ ቅመም አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፍቷል፡፡
አውደ ርዕዩን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አለሚቱ ኡሞድ የከፈቱ ሲሆን ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት እንደሚቆይም ተገልጿል፡፡
በአውደ ርዕዩ ሕብረት ስራ ማህበራት፣አምራቾች እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
የአውደ ርዕዩ ዋነኛ ዓላማ አገሪቷ ያላትን አቅም ማስተዋወቅ፣አምራቾች ልምድ ልውውጥና በሸማችና አቅራቢ መካከል የገበያ ትስስር መፍጠር መሆኑም ነው የተገለጸው።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ከቅመማ ቅመም የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግም የወጪ ንግድ እና የግብርና ኤክስቴንሽን ላይ ያሉ ችግሮችን በመለየት ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም ቅመማ ቅመም ላይ ትኩረት ሰጥተው ከሚሰሩ ግብርና ምርምር ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ባለሥልጣኑ ዘርፉን ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የቅመማ ቅመም ግብይት ጥራትና ቁጥጥር አሰራር ስርዓት እንዳልነበር የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ የአሰራር ስርዓት ተዘጋጅቶ እንዲጸድቅ መደረጉን አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪም የቡና እና ቅመማ ቅመም ክላስተር ድጋፍ አተገባበር፣የቅመማ ቅመም የዘር ስርዓት አተገባበር፣ኤክስቴንሽን አደረጃጀት ላይ ትኩረት ያደረጉ መመሪያዎች መዘጋጀታቸውንም ነው ዶክተር አዱኛ ያስረዱት።
የኢትዮጵያ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር በበኩላቸው ከአውደ ርዕዩ ጎን ለጎን በቅመማ ቅመም ዘርፍ ላይ ያሉ ችግሮች በሚመለከት ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ክልሎች ተሞክሯቸውን እንደሚያቀርቡ ጠቁመው፤ እንደዚህ ዓይነት ሁነቶች ዘርፉን ለማሳደግ ያላቸው ፋይዳ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
በአውደ ርዕዩ ላይ ከደቡብ ክልል ሀላባ ዞን የበርበሬ ምርት ይዘው የቀረቡት የመንቼኖ የገበሬዎች ኀብረት ሥራ ዩኒየን ተወካይ አቶ መሀመድ ሁሴን ለኢዜአ በሰጡት አወድ ርዕዩ የቅመማ ቅመም ውጤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እንድናቀርብ መሰል ዝግጅቶች እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ከአውደ ርዕዩ መክፈቻ ጎን ለጎን ውጤታማ የሆኑ ሴት አርሶ አደሮች የእውቅና አሰጣጥ መርሐግብር ተካሄዷል።