በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ መልሶ የተገነባው የጨርጨር ወረዳ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ መልሶ የተገነባው የጨርጨር ወረዳ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ጀመረ
አዲስ አበባ መጋቢት 8/2015 (ኢዜአ)፦ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ጉዳት የደረሰበትን የጨርጨር የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በ60 ሚሊየን ብር ወጭ መልሶ በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃቱን አስታወቀ።
ፕሮጀክቱ ከ15 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልጿል።
የመጠጥ ውሃ መልሶ ግንባታውን ያስጀመሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ሚኒስቴሩ በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የመልሶ ግንባታ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የጨርጨር የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በሶስት ወራት ውስጥ በተሻሻለ ሁኔታ አገልግሎት ማስጀመር መቻሉ "ትልቅ ስኬት" ነው ብለዋል።
የውሃ መሰረተ ልማቱ ከነዳጅ ፓምፕ ወደ ፀሐይ ኃይል በመቀየር ወደ አገልግሎት እንደገባ ጠቅሰው፤ ሕብረተሰቡም ለውሃ ፕሮጀክቱ እና ለሶላር ሲስተሙ ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሱልጣን ወሊ በበኩላቸው ከዋና መስመር በሚርቁ አካባቢዎች በነዳጅ ፓምፕ የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን በፀሐይ ኃይል የመቀየር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
የጨርጨር የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የፀሐይ ኃይል ፓኔል ለ25 ዓመታት አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በቀጣይ በመጠጥ ውሃ እና በመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን በሶላር ፓምፕ የመተካት ስራዎች እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ ተወካዮች በበኩላቸው መንግስት በአካባቢው እያካሄደ ያለውን የመልሶ ግንባታ ስራ አድንቀዋል።
ቀደም ብሎ ንጹህ ውሃ ባለመኖሩ ለተለያዩ ችግሮች ሲጋለጡ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆናቸው ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።