የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ረቂቅ ሕግ የዜጎችን የፍትሕ አገልግሎት ጥራት በሚያስጠብቅ መልኩ እየተዘጋጀ ነው - የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ - ኢዜአ አማርኛ
የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ረቂቅ ሕግ የዜጎችን የፍትሕ አገልግሎት ጥራት በሚያስጠብቅ መልኩ እየተዘጋጀ ነው - የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
አዲስ አበባ መጋቢት 8/ 2015 (ኢዜአ)፦ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ረቂቅ ሕግ የዜጎችን የፍትሕ አገልግሎት ጥራት በሚያስጠብቅ መልኩ እየተዘጋጀ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ የህግ፣ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ረቂቅ ሕግን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር ባቀረበው የማሻሻያ ምክረ ሃሳብ ላይ ምክክር አካሂዷል።
በምክክሩም ከቋሚ ኮሚቴው፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ የፌደራል ጠበቆች ማህበር፣ የረቂቅ ዝግጅት ባለሙያዎች እና ሌሎች የህግ ሙያተኞች ተሳትፈዋል።
በዚሁ ወቅት የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ወይዘሮ እጸገነት መንግስቱ፤ ለማሻሻል በዝግጅት ላይ ያለው የወንጀል ሕግ ከ1954 ዓ.ም ጀምሮ ከስልሳ ዓመታት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የወንጀል ሕጉም አስር የሚጠጉ መጽሐፍት እንደነበሩት ጠቁመው፤ የሕጉን ስፋት እና ይዘት መነሻ በማድረግም ሰፊ ግምገማ መደረጉንና ሰፊ መነሻ ሃሳብ መወሰዱን ገልጸዋል።
የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ረቂቅ ሕግ ዝግጅት ባለሙያዎችም በዝግጅት ሂደት ህዝብን በማሳተፍ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ምክክር መደረጉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የፌደራል ጠበቆች ማህበር የባለሙያዎች ቡድንም ረቂቅ ሕጉን በመዳሰስ መካተት ይኖርባቸዋል ያላቸውን ምክረ ሃሳቦች ማቅረቡን አንስተዋል።
ከማህበሩ የቀረበውን የረቂቅ ህግ ማሻሻያ ምክረ ሃሳብም ከቋሚ ኮሚቴው አባላት እና ከፍትሕ ሚኒስቴር የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ረቂቅ ሕግ ዝግጅት ባለሙያዎች ጋር ገንቢ ምክክር ተደርጓል ብለዋል።
በቀጣይም ለረቂቅ ሕጉ ግብዓት እንዲሆኑ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን በማካተት የዜጎችን የፍትሕ አገልግሎት ጥራት እንዲያስጠብቅ በማድረግ በተያዘው በጀት ዓመት እንዲጸድቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሕጉም ረዥም ዓመታት ያሳለፈ በመሆኑ የረቂቅ ሕግ ዝግጅቱ ዘመኑ የደረሰበትን የሕግ እና የቴክኖሎጂ እድገት ከግምት በማስገባት ከወቅቱ ጋር ሊሄድ በሚችል መልኩ እየተዘጋጀ መሆኑን አንስተዋል።
በረቂቅ ሕግ ዝግጅቱ ህዝቡን እና ለረቂቅ ህጉ ቅርበት ያላቸውን ተቋማት በማሳተፍ በይዘቱ ላይ ግልጽነት እንዲፈጠር በማድረግ የማስተካከያ ምክረ ሃሳብ መቀበል እንደተቻለ ገልጸዋል።
ቋሚ ኮሚቴውም በረቂቅ ሕጉ ማሻሻያ የሚፈልጉ ጉዳዮች ካሉ እንዲሻሻሉ በማድረግ የፍትሕ፣ የሕግና የሰላም ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በረቂቅ ሕጉ ከምርመራ፣ ከዋስትና፣ ከልዩ የወንጀል ምርመራ፣ ከቅሬታ ማስተላለፍ፣ ፍርድን እንደገና ከማየት፣ ከጊዜ ቀጠሮ፣ ከድርድር ፍትሕ ጋር የተያያዙ እና የዜጎችን እንግልት የሚቀንሱ አዳዲስ ድንጋጌዎች እንደተካተቱም ተናግረዋል።
የረቂቅ ህጉ ዝግጅት የባለሙያዎች ቡድንም የሚቀርቡ ጠቃሚ ምክረ ሀሳቦችን በማካተት በትኩረት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በምክክሩ የተሳተፉ የቋሚ ኮሚቴው አባላት፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ተወካዮች እና ረቂቅ ሕግ ዝግጅት ባለሙያዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ የፌደራል ጠበቆች ማህበር ባለሙያዎች በረቂቅ ሕጉ ላይ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።