ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ወራት ወደ ውጭ ከላከችው የቡና ምርት 787 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አገኘች

አዲስ አበባ መጋቢት 8/ 2015 (ኢዜአ)፦ በ2015 በጀት ዓመት  ያለፉት ስምንት ወራት ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ምርት 787 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ። 

የኮቪድ ወረርሽኝ፣ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና ዋጋ እየወረደ ቢመጣም ኢትዮጵያ የገበያ መዳረሻዎቿን በማስፋት በሰራችው ስራ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ባለስልጣኑ አስታውቋል። 

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ ሻፊ ዑመር ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በዓለም ገበያ የቡና ግብይት ሰላሳ ሁለት በመቶ  መውረዱን ተናግረዋል። 

በተለይ ኢትዮጵያ አብዛኛውን የቡና ምርቷን ወደ አውሮፓ ስትልክ ስለነበር የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በገበያው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል። 

መንግሥት ዓለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ የቡና ወጪ ንግድ ሪፎርም በማድረግ የገበያ መዳረሻዎችን የማስፋት ስራ ማከናወኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ  ወደ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ቻይና እና አውስትራሊያን ጨምሮ ወደ አዳዲስ መዳረሻዎች የቡና ምርቷን በስፋት መላክ ጀምራለች ብለዋል።

ይህን ተከትሎም የዓለም የቡና ገበያ ቢቀዛቀዝም በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት 143 ሺህ 762 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 787 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን በማንሳት።

ባለፈው ዓመት ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት ገቢ ጋር ሲነጻጸርም የ38  ነጥብ 5 በሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል። 

እንደ ኃላፊው ገለጻ የወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ማዘጋጃና ማከማቻ ቦታዎችን በማስፋት ጥራቱን የማስጠበቅ ስራ መሰራቱ ለገቢው መሳካት ሌላኛው ምክንያት ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባና ድሬዳዋ በተጨማሪ ጅማና ሀዋሳ ላይ ማዕከላትን በመገንባት ስራ ለማስጀመር እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው በቀጣይም ጊንቢ ላይ ለማስገንባት መታቀዱን ተናግረዋል።


 

በዚህም የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል ከአመራረቱ እስከ ፈጣን አቅርቦቱ ድረስ ሰንሰለቱን የጠበቀ የምርት ግብይት ለማካሄድ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ በማንሳት።

ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ የምርት ጥራቱን የማስጠበቅ በተጨማሪም ግብይቱን የማዘመንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር የማድረግ ስራዎች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት 302 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውሰዋል።

በቀጣይ ቡናን እሴት ጨምሮ በስፋት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም