ቀጥታ፡

የቦረና ህዝብ በድርቅ ምክንያት የገጠመውን አስቸጋሪ ጊዜ "በቡሳ ጎኖፋ" እና በወገናዊ የመረዳዳት እሴት እያለፈው ይገኛል- የአካባቢው አገር ሽማግሌዎችና ነዋሪዎች 

አዲስ አበባ መጋቢት 8/ 2015 (ኢዜአ)፦  የቦረና ህዝብ በድርቅ ምክንያት የገጠመውን አስቸጋሪ ጊዜ "በቡሳ ጎኖፋ" እና በወገናዊ የመረዳዳት እሴት እያለፈው ይገኛል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገርናቸው የአገር ሽማግሌዎችና ነዋሪዎች ገለጹ። 

በቦረና ዞን ለተከታታይ አምስት የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ባለመጣሉ ምክንያት በተከሰተው ድርቅ በእንስሳት ሃብት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፤ በዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች ለችግር ተዳርገዋል፡፡

በዚህም መንግስት ሰብዓዊ ድጋፍ በማቅረብ ህዝቡን እየደገፈ ሲሆን፤ መላ ኢትዮጵያዊያንም በቦረና የሚገኙ ወገኖቻቸውን ችግር ለማቃለል እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ 

በተለይም የክልሉ መንግስት ራሱ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪ በማቅረብ ያሰባሰበውን ሃብት ለህዝቡ በማድረስ ላይ ይገኛል። 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአገር ሽማግሌዎች ድርቁ በተለይ በእንስሳት ሃብት ላይ ጉዳት ማድረሱን ይናገራሉ፡፡

በሳር እና በውሃ ሃብት ይታወቅ የነበረው የቦረና መሬት በድርቅ በመመታቱ አርብቶ አደሩ በደረሰበት የሞራል ስብራት መጎዳቱን ነው አቶ ሊበን ጃተኒ እና አቶ ዶዮ ጉዮ የተባሉ የአገር ሽማግሌዎቹ የሚናገሩት።

አሁን ላይ  በቡሳ ጎኖፋ የመረዳዳት ባህል አመካኝነት ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ መላ ኢትዮጵያውያንም የቦረና ህዝብ የገጠመውን ችግር በመገንዘብ በወገናዊ አብሮነት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የክልሉ መንግስት ራሱ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር ቡሳ ጎኖፋ አማካኝነት ህዝቡ እርስ በእርስ እንዲረዳዳ እያደረገው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ዱቡልቅ ወረዳ የሚገኙ ወገኖችም በመንግሥትና አጋር አካላት እየቀረበላቸው የሚገኘው ድጋፍ ህይወታቸውን እንደታደገላቸው ተናግረዋል። 

የምግብ እህል፣ ውሃ፣ መጠለያ እና ሌሎች ድጋፎች እየተደረገላቸው መሆኑን አክለዋል።

ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያልተቋረጠ የሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበላቸው መሆኑንም ገልፀው፤ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የዱቡልቅ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ከድር አብዱልቃድር በበኩላቸው፤ በወረዳው በመንግሥት ብቻ ከ63 ሺህ በላይ ዜጎች ያልተቋረጠ ድጋፍ በማግኘት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ወገን ለወገን በሚል ከሰሞኑን በተጀመረው ንቅናቄም በአካባቢው ለሚገኙ ተጨማሪ  ከ7 ሺህ በላይ አባወራዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ መቻሉንም  ጠቁመዋል።

መንግስት በቦረና ዞን በችግር ወስጥ ለሚገኙ ከ867 ሺህ በላይ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ በማድረግ ላይ መሆኑን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም