ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ተጠልለው ለሚገኙ የሶማሊላንድ ስደተኞች የሚቀርበው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

አዲስ አበባ መጋቢት 8/2015 (ኢዜአ) የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያቀርቡ አጋር አካላት በኢትዮጵያ ተጠልለው ለሚገኙ የሶማሊላንድ ስደተኞች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የዓለም የምግብ መርኃ-ግብር ጥሪ አቀረበ።  

በኢትዮጵያ በሱማሌ ክልል ዶሎ ዞን ተጠልለው ለሚገኙ የሶማሊላንድ ስደተኞች 100ሺህ መድረሳቸው የዓለም የምግብ መርኃ-ግብር ገልጿል።

ከስደተኞቹ መካከል አብዛኞቹ ሴቶች፣ ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች፣ ህጻናት፣ ከፍተኛ ህክምና የሚያስፈልጋቸው አዛውንቶችና አካል ጉዳተኞች መሆናቸውም ተጠቁሟል። 

በኢትዮጵያ የዓለም የምግብ መርኃ-ግብር ተወካይ ክላውድ ጂቢዳር እንደገለጹት ግጭትን ሸሽተው በኢትዮጵያ የተጠለሉት የሶማሊላንድ ስደተኞች በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።

“አሁን እያቀረብንላቸው የምንገኘው በቂ ያልሆነ ድጋፍ ነው" በመሆኑም የምግብ አቅርቦቱ ይበልጥ ተጠናክሮ ለተጎጂዎች መዳረስ አለባቸው ነው ያሉት። 

በመሆኑም አጋር አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት። 

ሁኔታው በአንድ ጀንበር የሚቀየር ባይሆንም ሁሉም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ድጋፍ እንዲያደርግ አሳስበዋል። 

"ይህን ማድረግ ከቻልን ስደተኞቹ ወደ አገራቸው እስኪመለሱ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ማቆየት እንችላለን" ብለዋል። 

ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹን በመልካም ሁኔታ እየተቀበሏቸው መሆኑን አንስተው ምስጋና አቅርበዋል።

ነዋሪዎቹ በምስራቅ አፍሪካ በከፍተኛ ሁኔታ በድርቅ በተጎዳ አካባቢ ቢኖሩም ካላቸው ጥቂት ጥሪት ላይ በማካፈል ለጋስነታቸውን ማሳየታቸውን ጠቁመዋል። 

“የኢትዮጵያ መንግሥት መጠለያ ፍለጋ ወደ አገሪቱ ለሚገቡ ስደተኞች ለረጅም ጊዜ ሲያሳይ የኖረውን መልካም አቀባበል አሁንም አሳይቷል ያሉት ደግሞ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ተስፋሁን ጎበዛይ ናቸው። 

"ኢትዮጵያ ሰብዓዊና ተፈጥሯዊ ሁኔታዎችን ተቋቁማ ምላሽ በመስጠት ድጋፍ ፈላጊዎችን አስጠልላለች፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ለስደተኞቹ አስፈላጊውን ምላሽ እየተሰጠ ነው“ ብለዋል። 

የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን የኢትዮጵያ ተጠሪ ማማዱ ዲያን ባልዴ “አሁንም ኢትዮጵያውያን ጥበቃ ለሚሹ የሶማሊያ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው በራቸውን በመክፈት ያልተገደበ ልግስናቸውን አሳይተውናል” በማለት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም