በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በመጪው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የሚተከሉ 368ሚሊዮን ችግኞች እየተዘጋጁ ነው

ጭሮ መጋቢት 8/2015 (ኢዜአ) በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በመጪው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የሚተከል 368ሚሊዮን ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት አስታወቀ

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ሀላፊ አቶ አልይ ዳዲ ለኢዜአ እንደገለጹት እስካሁን በተከናወነ የችግኝ ዝግጅት ስራ 368ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በማዘጋጀት የእቅዱን 80በመቶ ማሳካት ተችሏል።


 

የችግኝ ዝግጅት ስራው በዞኑ በሚገኙ 15 ወረዳዎች ስር በሚገኙ 495 ቀበሌዎች እና በመንግስት ችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ረዘም ላሉ አመታት አዳዲስ ዛፎች ከመትከል ይልቅ ነባሩን ብቻ የመጠቀም አዝማሚያ እንደነበር ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል።

 

በዚህም በዞኑ አብዛኛዎቹ ወረዳዎች የደን ምንጣሮና የአካባቢ መራቆት አጋጥሞ እንደነበር አስታውሰዋል።

ካለፈው በመማር 'የአረንጓዴ አሻራ' መርሃ-ግብር ከተጀመረ ወዲህ ሕዝቡን በስፋት በማሳተፍ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት። 

በህብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ የተሰራው የተፋሰስ ልማት ስራ ዋና አላማ አካባቢውን አረንጓዴ ማላበስ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ በተካሄደ የተፋሰስ ልማት ስራ 288 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

 

እየተዘጋጁ ከሚገኙ ችግኞች መካከል ማንጎ፤ አቮካዶ፤ ጊሽጣና ቴምር እንዲሁም ለደን ልማት የሚውሉ ዛፎችና የእንስሳት መኖ ይገኙበታል።

ቀደም ባሉት ዓመታት በተራቆቱና በጎርፍ የተሸረሸሩ ተራሮች ላይ የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠናቸው ጥሩ መሆኑን ገልጸው አካባቢው በአረንጓዴ ከተሸፈነ በኋላ የዱር እንስሳት እየተመለሱ ነው ብለዋል፡፡

 

ባለፉት ዓመታት በዞኑ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከተተከሉ ችግኞች መካከል 88በመቶ የሚሆነው መጽደቁን አረጋግጠዋል።

በችግኝ ተከላው 1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የሚሳተፉ ሲሆን 200ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ ይካሄዳል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም